መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Monday, August 30, 2010

ወመኑ ዘየኃሥሶ ጥበበ ለዝ ዓለም? 1 ቆሮ 1፦20-23

የዚህን ዓለም ጥበብ የሚሻው ማነው?

በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ የመንግስቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ ከተጠራን ከእኛ ከወንድሞቻችሁና ከእኅቶቻችሁ ፤

የጥበብን ፋና ስለመግዛት ፤ የድንቁርናን ጨለማ ስለማራቅ ፤ ራስን ፣ ቤተሰብንና ሀገርን በእውቀትና በሀብት ስለማሳደግ ምክንያት በየትምህርት ተቋማቱ ሆናችሁ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥም ለምትጠሩ ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

Tuesday, August 24, 2010

እናንተን ... " የሴት ልጅ " አሏችሁ?

እናንተን ... " የሴት ልጅ "  አሏችሁ?

' የሴት ልጅ ' ተብላችሁ
በእጅጉ የከፋችሁ
እጃችሁን ... እስቲ ልያችሁ
/ በቃ! ... በቃ! ... በጣም በዛችሁ /
ይኼ መስፈርት ያሻዋል ... ልብ ብላችሁ አድምጡ
ያገባናልም ስትሉ ... ቶሎ ወደ ዳር ውጡ።
*****************************
በመጀመሪያ ...
በኑሮ ትግል ያልተረታ
በውሽንፍሩ ያልተፈታ
የእናቱ ወኔ ያለው 
እርሱ ካለ እንየው
የለም?
******************************
በመቀጠል ...
ማጣት ያላሟጠጠው
' ልጄ ... ልጄ ... ' የሚያስብለው
ፍቅሯ ያለው
እርሱም ካለ እንየው
እርሱም የለም? ...
*******************************
እህ ...
ታዲያ ለምን ከፋችሁ?
እናንተ ' የሴት ልጅ ' አይደላችሁ።

Thursday, August 19, 2010

ዝም ያለ ... ዝም! አለ

ዝም ያለ ... ዝም! አለ

' ዝም
አይነቅዝም ' ሲሉት
... ዝም ሲል
' ዝምታ 
ወርቅ ነው ' ሲሉት 
... ዝም ሲል
' ዝም ባለ አፍ 
ዝምብ አይገባበትም ' ሲሉት
... ዝም ሲል
ዝም! አረጉት አሉ
ወደህ በገባህ እያሉ።

10/01/98
ዲላ

መወለድ ቋንቋ ነው።

መወለድ ቋንቋ ነው።

መለያየት ነግሶ ... ብልጥነት አይሎ
መቻቻል ተረስቶ ... ሞኝነት ተብሎ
                    ' ባዳማ ባዳ ነው ' ... ተዘውትሮ በጣም
                    ' ዘመዴ ዘመዴ ' ... ማለት አያዋጣም።
ልብ ተራርቆ ... መግባባት ከታጣ
ዘመድም ባዳ ነው ... መላቅጡን ያጣ
                     ዘር መቁጠር ግን ቀርቶ ... መመቻቸት ቢኖር
                     መወለድ ቋንቋ ነው ... አይደለም ቁምነገር።


18/02/98
አዋሳ

ደብረ ታቦር

Wednesday, August 18, 2010

የፈጣሪን መኖር እንዴት ማወቅ ይቻላል?

የፈጣሪን መኖር እንዴት ማወቅ ይቻላል?

ሰው በልዩ ልዩ ተፅዕኖ ምክንያት በራሱ ፈቃድና ውሳኔ ካልተወው በቀር ፤ የፈጣሪን ሀልዎት ( መኖር ) ፈልጎና መርምሮ የሚያውቅበት እውቀትና ችሎታ ፤ ደግና ክፉን ለመለየት የሚያስችለው ሕገ - ልቦና ( የሞራል ሕግ ) በተፈጥሮ እንደተሰጠው የታመነ ነው። በሞራል ሕግ - በምርምር የፈጣሪን መኖር ማወቅ አይቻልም በማለት በነፃ ፈቃዳቸው በድፍረት ወስነው የሃይማኖትን ነገር ፈፅሞ እንዳያስቡ የኅሊናቸውን በር የዘጉትን ሰዎች ወደጎን ትተን ፤ በመጀመሪያ ሥነ-ፍጥረትን ቀጥሎም ሰብአዊውን ፍጡር ፤ ሰውን ፦ በተለየ መልኩ በመመርመር እንዴት የፈጣሪን ሀልወት ማወቅና ፤ መረዳት እንደሚቻል እነሆ ፦

የሥነ-ፍጥረትን ገጽታና ሁኔታ ፤ አሰራርና አካሄድ በመመልከት የማያደንቅ ሰብአዊ ፍጡር አይኖርም። በአጠቃላይ የሥነ-ፍጥረትን ውበት ፣ የአፈጣጠሩን ሥርዓት ፣ በቀን የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት፣ በሌሊት የጨረቃዋን ድምቀት ፀጥታና ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ በተረጋጋ ኅሊና ለሚያስተውለው ሁሉ የመገረም ስሜት ያድርበታል። ከበላያችን ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የተዘረጋው መጨረሻ የሌለው የሰማዩ ስፋትና ጥልቀት ፤ በሌሊት የሚያብረቀርቁት ከዋክብት ብዛት ፤ የአቀማመጣቸውና የእንቅስቃሴያቸው ሥርዓት ፣ የዘመናት መፈራረቅና ሌሎችም የተፈጥሮ ክስተቶች እጅግ ያስደንቃሉ። በተለይም በምድራችን ዙሪያ የሚገኙት ሕይወት ያላቸው ለምለም እፅዋት ፣ በእግር የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ፣ በክንፍ የሚበሩ አእዋፍና የሌሎችም አፈጣጠር በየወገናቸው ሲጠና ይልቁንም የሰዎች ልጆች ረቂቅ ተፈጥሮ ሲታይ በአጠቃላይ የሥነ-ሕይወት ክስተት ጉዳይ ሲመረመር አስተዋይ ኅሊና ያለውን ሁሉ ያስጨንቃል ፤ ያስጠብባል።

Monday, August 16, 2010

መሸ? ፤ ነጋ?

መሸ? ፤ ነጋ?

ልጆቹ ... ልጆቹ
እኒያ ጨቅላዎቹ
ኩኩሉ አኩኩሉ ... እየተባባሉ
ምሽትና ሌቱን ... ቶሎ ያነጋሉ።
ወዲያው ደግሞ ሲያድጉ ... ኩኩን ሲዘነጉ
        ...ጭንቅ ይላቸዋል ...
የቀኑ አመሻሸት ፤ የሌቱ አነጋጉ።


29/10/97
ዲላ

Wednesday, August 11, 2010

ከማን ታንሳላችሁ? iii

ከማን ታንሳላችሁ? iii

እነኛ ...
ዛሬ ሊያወጉ
አውግተውም ሊያዋጉ
ተዋጉ።
እናንተም ... 
ነገ እንድታወጉ
አውግታችሁም እንድታዋጉ
ጠብቃችሁ ተዋጉ i i i


09/01/98
ዲላ
( በዘር ምክንያት ለምትዋጉት )

ብልጠት ወይስ ሞኝነት?

ብልጠት ወይስ ሞኝነት?

የምኞት ድንበር ሲጣስ
          ራስ
ሁሉን አድራጊ ንጉስ
         ዐይን
አሁንም አሁንም የሚያይ
ሽቅብ ወደላይ ወደላይ።
****************
ሽቅቡን መውጣት መጀመር
     የማይገፋ ነገር
ድንገት ከጫፍ  ቢደረስ
ያሰቡት ከልብ አይደርስ።
****************
ይህን ጊዜ
ትካዜ።
***************
ተመልሶ ለመውረድ
አልቦ መንገድ
መንገዱ ቢኖር
አቅምና መላ ችግር።
**************
እንዲህ ... ውጥንቅጡ የወጣ ጊዜና
'እርሱ ... እግዚአብሔር ነውና
ያሻውን ፤ የፈቀደውን ... ያድርግ ' ማለት
ብልጠት ወይስ ሞኝነት?


22/09/2001
አ.አ

Friday, August 6, 2010

" የበላም ለራሱ ...የጾመም ለራሱ " ?

" የበላም ለራሱ ...የጾመም ለራሱ " ?

የበላ ... ለራሱ በላ
* * * * * * *
የበላ ... ሆዱ ሞላ
ሆዱ የሞላ ... ለስጋ ፈቃዱ አደላ
ለስጋ ፈቃዱ ያደላ ... ለነፍሱ ሆነ ተላላ
ለነፍሱ የሆነ ተላላ ... ከፈጣሪው ተጣላ
ከፈጣሪው የተጣላ ... እርሱ በሲኦል እሳት ሊበላ
               ጦሡ ተረፈ ለሌላ።
                 * * * * * * *
የጾመ ... ለራሱ ጾመ
* * * * * * *
የጾመ ... ስጋው ደከመ
በስጋው የደከመ ... የነፍሱን ፈቃድ ፈፀመ
የነፍሱን ፈቃድ የፈፀመ ... በፈጣሪው ፊት ቆመ
በፈጣሪው ፊት የቆመ ... ስለምግባሩ በመልካም ሁሉ ተሾመ
          ስለ'ርሱም ... ሌላው ካገኘው ደዌ ታከመ።

30/11/2002
Tromso, Norway

Thursday, August 5, 2010

ሊያሳስበን የሚገባ ሌላ ጉዳይ ...


በስመ ሥላሴ አሜን።
የቤታችንን ችግር አስመልክቶ  የተለያዩ ነገሮችን  በተለያየ መንገድ  ከተቆርቃሪዎችም ሆነ ግድ ከሌላቸው ወገኖች ብዙ ሰምተናል ... ከአንዳንዶቹም ጋር አብረን መክረናል ... ችግር ፈጠሩ ያልናቸውን አካላትንም  ኮንነናል ፤ ወቅሰናል ... መፍትሔ ስለምንለውም ነገር ብዙ ብለናል ... ነገር ግን አሁን በፊታችን ተገልጦ የምንጯጯህበት ይህ የቤተ-ክህነት ችግር እኛ ባሰብነውም ይሁን በሌላ ዘዴ ቢፈታ ወይም የተፈታ ቢመስል  እንኳ ትቶት ሊያልፈው ስለተዘጋጀው ጠባሳ ስንቶቻችን እናውቃለን?
በምንኖርባት በዚች አለም መሪዎች በተመሪዎች ላይ ቀንበር ሲያከብዱ ፤ ግፍን ሲያደርጉ ተመሪዎቹ በመሪዎቹ ላይ መነሳታቸው ፤ በተወሰኑትም መስዋዕትነት ሌሎቹ ነፃነታቸውን እንደሚያገኙ ታሪክ ምስክር ይሆናል ፤ ... ነገር ግን ይህን መሰሉ ክስተት የሚሰራው በአለም ነው! ... ምንም እንኳ እኛ ምዕመናን በአለም ውስጥ የምንኖር ቢሆንም ... በእግዚአብሔር ቤት አካሔዱ የተለየ ነው ... ሊለይም ይገባዋል ... ምክንያቱም አልቻለን እያለ ቢቸግረን ነው እንጅ ልንፈጽመው የምንወደው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ነውና ... ሀገራችንም በሰማይ ነውና ... በመሆኑም የቤተ-ክህነት ችግር መፍትሔ በምስኪን ምዕመናን መስዋዕትነት ወይም ዋጋ ሊታሰብ አይገባውም  ... ለዚያውም መስዋዕት ስለሆኑበት ነገር በውል በማይረዱበት ሁኔታ ...