መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Monday, September 20, 2010

የመስጠትና የመቀበል ሥሌት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የመስጠትና የመቀበል ሥሌት

የሰውን ልጅ የኑሮ ዑደት ፤ ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የመስጠትና የመቀበልን ያህል ሚና ያለው አንዳች ነገር ፈልጎ ማግኘት እጅጉን አዳጋች ነው። የሥነ-ፍጥረትን አሰራር ፣ አካሄድ ፣ እና አኗኗር በማስተዋል ለተመለከተ ሰው ፤ የዚህ ዓለም ፈጣሪና መጋቢ እግዚአብሔር አምላክ ፤ ዓለሙን በዚህ የመስጠትና የመቀበል ሥሌት እንዳፀናው ለመረዳት አይቸግርም ፤ ለአብነት እንኳ  የሰውን ልጅ የአተነፋፈስ ሥርዓት ብንመለከት ፤ ወደ ውስጥ የምናስገባውን ኦክስጅን ለመቀበል ምንም ያገለገለና የተቃጠለ ብንለው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን መስጠታችን ( ማስወጣታችን ) ድርድር የማያስፈልገው ነው ፤ ባንጻሩም ዕፅዋትና አዝርዕትም ቢሆኑ ፤ በፋንታቸው ምግባቸውን ለማዘጋጀት እንደ አንድ ግብዓት የሚያስፈልጋቸውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ለመቀበል ኦክስጅንን መስጠት ይኖርባቸዋል። ... ይኸስ ባይሆን ኖሮ ሁሉን ሊያደርግ የሚቻለው ፈጣሪ ፤ በየጊዜው ፦ በየዘመኑ ለሚኖሩ ሰዎች እና ዕፅዋት እንደ ልካቸው ( ብዛታቸው ) የሚያስፈልጋቸውን ፤ ለዚህን ያህል ሰው ይህንን ያህል ኦክስጅን ፣ ይህንንም ያህል ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ፤ ለዚህን ያህል ዕፅዋትም ... እያለ እየሰፈረ እና እየለካ ባዘጋጀ ነበር ፤ ነገር ግን ፈቃዱ ለአንዱ መኖር የሌላውን ህልውና ግድ የሚል ፤ አንዱ እንዲቀበል ለሌላው መስጠትን ቅድመ ሁኔታ ያደረገ ፤ አንዱ ለሌላው ፣ ሌላውም በሌላው ላይ ያለውን ተደጋግፎት የሚጠይቅ ፤ ... ነው።

በቅዱስ መጽሐፍ ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመስጠትንና የመቀበልን ሥሌት በተለያዩ ሀገራት ለተለያዩ ሰዎች እንዳስተማረና ይኼውም ትምህርቱ የዘለቃቸውና የተረዳቸው የተጠቀሙበትም በፊልጵስዩስ የነበሩት ሰዎች ብቻ እንደነበሩ ተጠቅሶ አለ። " ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተክርስቲያን በመስጠትም ቢሆን በመቀበል ከእኔ ጋር እንዳልተባበሩ እናንተ ታውቃላችሁ " ፊሊ 4 ፦ 15 .... እኒህ በጥንቷ ግሪክ ሰሜናዊ ጫፍ ፤ በመቄዶንያ አውራጃ ትገኝ በነበረችው  ፊልጵስዩስ የነበሩ ሰዎች ይህን የመሰለውን ምስክርነት ከታላቁ ሐዋርያ ያገኙት ፤ ሐዋርያው በሮም ሀገር የቁም እስረኛ በነበረበት ወቅት ልከውለት ሥለነበር አስተዋፅዖ ምክንያት ነው። ... ለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከተላከለት አስተዋፅዖ ላገኘው ጥቅም ምስጋና ፤ ይኸውም አስተዋፅዖዋቸው እንዳይቋረጥበት ሰግቶ ይህንን ተናገረን? ... እንዲያውም! ... ይልቁንስ ከበጎ ሀሳባቸው የተነሳ ሁሉ ካለው አምላክ ዘንድ በረከትን እንደሚያገኙ አስቦ ተናገራቸው እንጅ ፤ ይኼውም " ይህንም የማነሣሣው ስጦታችሁን ፈልጌ አይደለም ፤ በእናንተ ላይ የጽድቅ ፍሬ ይበዛ ዘንድ ፈልጌ ነው እንጅ " ፊል 4 ፦ 17 ባለው ይታወቃል። ... በዚህ ዘመንም ሰዎች በተለያዬ ሁኔታና መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች ተነሳስተውና ተገፋፍተው አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። ... ለመሆኑ ከሚሰጡት መካከል ... ስንቶቹ  ደጅ ተጠንተው ሰጡ? ... ስንቶቹስ ይህን አደረጉ ፤ ይህንን ደግሞ ሰጡ ፤ አጨብጭቡላቸው ፤ እልል በሉላቸው መባልን ሽተውና ስማቸው በአደባባይ እንዲጠራ ፈልገው ሰጡ? ... ስንቶቹስ ባለማስተዋልና በክፉ ብልጣብልጥነት ፤ ዘርዝረው የበተኗት አንድ ብር አንድ ሽህ እንድትወልድ ሰጡ? ... ስንቶቹስ እንደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ባለ መልካምነት ፤ የሚሰጡት ገንዘብ እግዚአብሔርን ሊደጉመው ፤ የሚያመጡት እጣን ከመዐዛው መልካምነት የተነሳ ሊያሸተው ፤ የሚያገቡት ጧፍም ጨለማውን ሊያርቅለት ሳይሆን ፤ የሰጡትን ከሰጡበት በጎ ኅሊና ( ሀሳብ ) የተነሳ የእግዚአብሔርን በረከት ሽተው ሰጡ? ... ቤት ይቁጠራቸው። ... የመስጠትና የመቀበል ሥሌቱ የገባቸው የፊልጵስዩስ ሰዎችስ ' እኛ በጫና ያይደለ በውድ ያለንን ደስ እያለን እንሰጣለን ፤ አንተ ደግሞ ለእኛ ምን ፤ መቼ እንደሚያስፈልገን ታውቃለህ ፤ በጊዜህም ታደርግልናለህ ' በሚል እምነት ሰጡ።

Wednesday, September 1, 2010

እንዲህም ብሎ ትዕግሰት እቴ i

እንዲህም ብሎ ትዕግሰት እቴ i

 ተቆርጦ ቀርቶ ... መሃል ገብቶ
ተከቦ አይቼው ... መውጫ አጥቶ
ታገስኩኝ ይላል ... አፉን ሞልቶ።