መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Saturday, December 10, 2011

ቀውጢዎች


ቀውጢዎች

ከቀውጢ የተወለድን
ቀውጢዎች
ቀውጢ አገር ያበቀለን
ቀውጢዎች
ቀውጢ ዘመን ያሳለፍን
ቀውጢዎች
ብንቀውጥ … ብናስቀውጥ
ብንቃወጥ … አይቀወጥ!!!
ነንና  የቀውጢ ልጆች
ቀውጢዎች
ቀውጢ ምትኮች።


(የትውልድን ቅብብሎሽ ዋጋ ለሚያሳንሱ ሁሉ)
ይህም ሲባል «እኛ ምን ይፈረድብናል?» የሚል አጉል ስንፍና ውስጥ ለመክተት ሳይሆን ቅብብሎሹን በመረዳት አስፈላጊውን ዋጋ ከፍሎ ቀጣዩን ትውልድ ማስተካከል ያለውን ተገቢነት ለማሳሰብ ነው።

Wednesday, December 7, 2011

መቅድም

መቅድም

ከዚህ አጭር ሀተታ በታች የምትመለከቱት ጽሑፍ ፤ በኢትዮጵያ ሥነፅሑፍ ታሪክ ውስጥ ገናና ከሆኑት ደራሲያን መካከል አንዱ የሆኑት ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የዕውቀት ብልጭታ በተሰኘ መጽሐፋቸው መግቢያ መቅድም አድርገው የጻፉት ነው። የተከበሩ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ጥቅምት ፳፫‚ ፲፱፻፱ የተወለዱ ሲሆን ፤ የቤተክህነትን ትምህርት ካገባደዱ በኋላ በአሊያንስ ፍራንሴዝና በላዛሪስት ሚስዮን ዘመናዊ ትምህርትን ተከታትለዋል። የግሪክን ፣ የእንግሊዝን ፣ የፈረንሳይን ፣ የጀርመንን ፣ የሩስያንና የጣልያንን በርካታ መጻሕፍት ከመረመሩም በኋላ ሃያ ስድስት መጻሕፍትን ለወገኖቻቸው ያበረከቱ ሲሆን ፤ በድርሰቶቻቸው ውስጥ የሚታዩት የሀሳብ አገላለጾች ፣ ቃላትና ዘይቤዎችም ኋላ ለመጡ ደራሲያን የነበራቸው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ይህንንም፥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለድንቅ ተግባራቸው በ፲፱፻፺ ዓም የክብር ዶክተርነት ክብርን በሰጠበት ወቅት “ … በተለይ ከ፲፱፻፶ዎቹ ወዲህ የተነሱ በርካታ ደራሲያን ፤ የርሳቸውን ድርሰቶች አንብበው ፣ በርሳቸው ድርሰቶች ሥነጽሑፍን አውቀውና አጣጥመው ደራሲ ሊሆኑ በቅተዋል።” በማለት ምስክሩን ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ እኒህ ታላቅ ደራሲ ትኩረታቸውን ሕጻናትና ልጆች ላይ ያደረጉ ፤ ግብረ ገብ የሚያስተምሩ ፣ ስለወገንና ሀገር ፍቅር የሚሰብኩ እና የዕውቀትና የሥራ ጠቀሜታን አጉልተው የሚያሳዩ አያሌ የሥነጽሑፍ ሥራዎችን አበርክተዋል።   

ይህን መቅድም ባነበብሁት ጊዜ ሁሉ ፤ ለሕጻናቱ ስሱ መሆናቸው … ለሕጻናቱ ያላቸው ከበሬታ … ባልደከሙበት እንዳያመሰግኑዋቸው ሕጻናቱን ግድ የሚሉበት ሞራል … አልፎ ተርፎም ክብርና ምስጋና ለሚገባው ክብርና ምስጋናን እንዲሰጡ ለሕጻናቱ ግብረ ገብ የሚያስተምሩበት አግባብ … እንዲሁም ለቀጣይ ትውልድ ጠቃሚ የሆነ ሥራን ስለመስራት ለሕጻናቱ ኃላፊነትን የሚሰብኩበት መንገድ ልቤን አንዳች ሀሴት ይሞላዋል … እነሆ፥ እኔን ደስ ያሰኘኛልና እናንተንም ደስ ቢያሰኛችሁ  ጻፍኩላችሁ ….  እነሆ፥ እኔን መደነቅ ውስጥ ይጥለኛልና ቢያስደንቃችሁ ጻፍኩላችሁ … እነሆ፥ የዛሬን በትላንት ሳየው ይቆጨኛልና ቢቆጫችሁ ጻፍኩላችሁ … እነሆ በደራሲው አምሳል ለሕጻናት ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን መስራት ቢከብደን በስራዎቻቸው ሕጻናቶቻችንን ማስተማር አይከብደንምና ስለማስታወስ ጻፍኩላችሁ ….    



መቅድም

Tuesday, December 6, 2011

ሁሉም የሆነ ነው

ሁሉም የሆነ ነው

ሁልጊዜ አዲስ ነገር ምነው መወደዱ?
ሁሉም እያረጀ አይቀርም መሄዱ።

ሰሎሞን ብሎናል ደጉ ተመልካች
አዲስ ነገር የለም ከፀሐይ በታች።

ጄንጂስካን ቲሙርሌንግ አቲላ ቄሳር
ሻርልክ ናፖሊዮን ትልቁ እስክንድር
አልፎ አልፎ በተራ በቅደም ተከተል
ዓለምን በሙሉ ይዘው በመጠቅለል
በሰይፍ በጎራዴ ፍጥረት እያመሱ
በብዙ ጭካኔ ደም እያፈሰሱ
ይመስላቸው ነበር ሠርተው የፈጸሙ
ዳሩ ግን አልሆነም በከንቱ ደከሙ።

ዓለም ሳትለወጥ ባህልዋን ሳትረሳ
እስር ትገባለች ወዲያው ተመልሳ።

የታሪክን ጉዞ ያልተገነዘበ
ሁሉንም ያደንቃል እያጨበጨበ።

ለመጭው ሳያስብ ላላፊው ሳያዝን
በልማድ ይኖራል ጅል ሳያመዛዝን።

ብልህ ያስተውላል አይደናበርም
መሄድ መመለሱን አይጠራጠርም።

Friday, December 2, 2011

በ'ኛ ዘመን

በ'ኛ ዘመን


መቆንጀት ማስጠላት … ማፈርና መኩራት
መሄድ አለመሄድ … ማበድ አለማበድ
መጎበዝ መደደብ … ማሰብ አለማሰብ
መኖር አለመኖር … የትርጉሙ ነገር
             
             ወዳጅነት ፈጥሮ … ጋብቻ መስርቷል።
             ሁሉም ‘ጨዋ’ ሆኖ … የሚያፋታም ጠፍቷል።

እያሰቡ አለማሰብ … እየጎበዙም መደደብ
እየኖሩ አለመኖር … መደንበር መደናገር
            ተወልደዋል።
‘ፍቅር' አሙቀዋል … ‘80' አጽንተዋል።


ማን ያውቃል?
የልጅ ልጃቸውንም … ያሳዩን ይሆናል።
የ‘ሳት ልጅ አመድ ዓይነት … የወላድ መካንም ይሆኑ ይሆናል።
እንዳሻቸው እንደፈለጉም ይሆኑ ይሆናል።
ማን ያውቃል?


ኦላ መገኖ!


ኦላ መገኖ=ጌታ ያውቃል (ጌዴዎኛ)

ግን ግን … በዚህች ቅድስት ሀገር ነውርና ነውረኛ ከጊዜ ወደጊዜ ለመበራከቱ ምህኛት ተብዬው ምን ይሆን?