መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Wednesday, July 21, 2010

" በእምነት ስላልተዋሃደ ... አልጠቀማቸውም " ዕብ 4፦2

" በእምነት ስላልተዋሃደ ... አልጠቀማቸውም " ዕብ 4፦2

በስመ ሥላሴ አሜን።

በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ከእኔ ከወንድማችሁ ፦ የክርስቶስ ኢየሱስ የመንግስቱ ወራሾች ትሆኑ ዘንድ ለተጠራችሁ ለናንተ ፦ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ፤ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ወንድሞች ሆይ ፦ የነፍሳችንን ድኅነት ፤ የልጅነትን ክብር ፤ ተስፋ ስለማድረግ ምክንያት በቤተክርስቲያን ጥላ ስር በእምነት የምንኖር ነንና እራሳችንን ከእግዚአብሔር ቤት ሕግና ሥርዓት በታች እናስገዛለን ፤ ታዲያ ምንም እንኳን በልቦናችን ያለው ይህ የእግዚአብሔር ሕግ መልካም ቢሆንም (ሮሜ 7 ፦ 22) ከሥጋችን ደካማነት ፣ ከዲያቢሎስም ውጊያ የተነሳ የኃጢአትን ሕግ እንመለከታለን። እንዲህም ስለሆነ እባብ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳሳታት ለሥጋ በመድከማችን ምክንያት አሳባችንና ፈቃዳችን ከክርስቶስ የዋህነትና ንፅህና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እሰጋለሁ። ... ወዲህም ደግሞ " እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን " (ሮሜ 8 ፦ 28) ስለተባለው የተስፋ ቃል ከስጋቴ አርፋለሁ ... ቢሆንም ግና አሁንም መልሼ እሰጋለሁ ... እግዚአብሔርን ከሚወዱት ከምርጦቹ መካከል አንሆን ይሆን ብዬ ... ምክንያቱስ ፦ እርሱን የሚወዱ ፍለጋውን ይከተላሉ ተብሏልና ... ታዲያ ስንቶቻችን ጎዳናውን ተከትለናል? ... እግዚአብሔርን መውደዳችንስ ወዴት አለ? ... እንዴትስ እየገለፅነው ነው? ...


ትዕዛዛትን በመፈፀም ስለሚገለጥ እግዚአብሔርን የመውደድ ነገር ከማንሳታችን በፊት ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ እንዲባል ለትዕዛዛቱ በፍቅር እንድንገዛ ስለሚያደርገን እምነታችን እንነጋገር ... ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው " አሚንሰ መሰረት ይእቲ ወካልዐኒሃ ሕንፃ ወንድቅ እሙንቱ - እምነት መሰረት ናት ሌሎቹ ግን ሕንፃና ግንብ ናቸው። " እንዳለ ... ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የእምነትን ነገር አጉልቶ ባቀረበበት አንቀጹ " ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ... ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው አስቀድሞ እግዚአብሔር እንዳለ ፤ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጣቸው ሊያምን ይገባዋል " እንዳለ። ወንድሞች ሆይ ፦ የእምነትን ነገር ማንሳቴ በእግዚአብሔር ላይ ያላችሁን እምነት ስለመፈታተን አይደለምና ቅር እንዳንሰኝ ... በሃይማኖት ስትኖሩ እራሳችሁን መርምሩ እንደተባለ መታመናችን እስከምን ድረስ እንደሆነ እራሳችንን እንጠይቅ እንጅ

ወገኖቼ ፦ እዚህ ላይ በታላቁ መጽሐፍ ፤ በመጸሐፍ ቅዱስ ፤ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ዕብራውያን ሰዎች በላከው መልዕክቱ ላይ ፦ አስቀድመው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንና ደቀመዛሙርቱን ፤ ወንጌልን ስለማስተማራቸው ምክንያት ይቃወሟቸውና ይጠሏቸው ስለነበሩ ፤ ከዚያም ጌታ ካረገ በኋላ በሐዋርያት ቃል የሚደረገውን ተአምራት ባዩ ጊዜ ወደ ማመን ስለመጡ ዕብራውያን እና አህዛብ የተነገረውን ቃል ፦ " ... የምስራች ተሰብኮላቸዋል ፤ ነገር ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ሥላልተዋሃደ አልጠቀማቸውም። " (ዕብ 4 ፦ 2) ... የሚለውን ጠቅሼ ልናገር እወዳለሁ ፤ በዚህ ዘመን ላለው ለእኛ እምነት ተምሳሌት ይሆናልና። ... ሐዋርያው ስለነዚህ ሰዎች የእምነት ጉድለት እንዲህ ማለቱ እንደ አባቶች ትርጓሜ ፦ እምነታቸው ሕገ-ወንጌልን ለሕገ-ኦሪት ተጨማሪ ሕግ በማድረግ ፤ ሕገ-ኦሪትን ከሕገ-ወንጌል አብልጠው መጠበቃቸው ሳይቀር ስለነበረ ነው።

ታዲያ በዚህ በእኛ ዘመንም የብዙዎቻችን እምነት እንዲህ ከላይ እንደተወቀሱት ሰዎች አይነት ፤ ጎዶሎና ፤ የማይጠቅም የሆነ ነው። ... እንዴት ቢሉ ፦ በእግዚአብሔር ከመታመናችን ጋራ አዳብለን የያዝናቸው በአይነት እና በመጠን እንደጣት አሻራዎቻችን የተለያዩ ሚጢጢ የየግል " እምነቶች " አሉንና። ... እኩሌታችን ፦ በእግዚአብሔር የምናምነው ፤ ገንዘብ ፦ የማይናቅ ጉልበት እንዳለው ከማመን ጋራ ነው። ... እኩሌታችንም የወፋፍራም ዘመዶቻችንን ትከሻ ከመደገፍ ጋራ ፤ ሌሎቻችንም ለራሴ ራሴ አውቅላታለሁ ከሚል ትምክህት ጋራ ፤ ሌላም ሌላም ... ጋራ ነው። ስለዚህም በእግዚአብሔር መታመናችን ፣ ለርሱ መገዛታችን በሌላ አላስፈላጊ ቆሻሻ ተመርዟልና አይጠቅመንም። ... እዚህ ላይ የእግዚአብሔርን የምህረትና የቸርነት ሥራ እንደሌለ ፤ እንደዚህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያለን ሰዎች ፈፅሞ የተጣልንና ፈላጊ የሌለን አስመስዬ ማቅረቤ አይደለም ፤ ... የድርሻችን የሆነውን ፤ ከእኛ የሚጠበቀውን አጉድለናል ለማለት ፈልጌ እንጅ ...

ወንድሞቼ ሆይ ፦ ይህ ያለንበት ዘመን ለራስ ፣ ለወገን ፣ ለሀገርና ለቤተክርስቲያን መልካም የሆነውን ለማድረግ ከመቸውም ጊዜ በተለየ ታላቅ ተጋድሎን የምንፈፅምበት ስለሆነ ራሳችንን በመንፈሳዊም ሆነ ሥጋዊ ትጥቅ ልናዘጋጅ ያስፈልገናል። " ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ ፤ እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ " (ኤፌ 6 ፦ 13) እንደተባለ ... መንፈሳዊ የተባለና ለመንፈሳዊ አላማ የተመረጠ ሰው አካሄዱ ሁሉ መንፈሳዊ ሊሆን ይገባዋልና ከአምላኩ ሕግ ፣ አኗኗር ፈቀቅ ከማለቱ የተነሳ ፤ ከራሱም ሥጋዊ ደማዊ ተግባር በመነጨ ከሚመጣበት መከራና ስቃይ ሁሉ ሊላቀቅ የሚችለው እግዚአብሔር በሚወደውና በሚፈቅደው አካሄድ ብቻና ብቻ ነው። ... እርግጥ በተለያዩ ጊዜያት አንገብጋቢ የሆኑ ሀገራዊና ቤተክርስቲያናዊ ችግሮች ሲከሰቱ እናያለን ፤ እንሰማለን ቢሆንም ሀገርና ቤተክርስቲያን ከገቡበት ችግር እንዲወጡ የበኩላችንን ለመስራት አስቀድመን እኛ ልንሰራ ያስፈልገናል ... ችግሩን በመፍታት ሂደት ውስጥም እጃችንን የምናስገባ ከሆነ ሐዋርያው እንዳለ እንድንፀና በሁሉ የተዘጋጀን ልንሆን ይገባል።

እንዲህም ስለሆነ ፦ በእግዚአብሔር እናምናለን የምንል ሁላችን የደስታችንንም ሆነ የሀዘናችንን ወራት ከእርሱ ጋር ልናሳልፍ የሚያስፈልገን ነውና በዚህ ወቅትም ፈጣሪ በጥበቡ በራሳችን ምክንያት ከሆነብን ክፉ ነገር እንዲያወጣን በተለይም ደግሞ በዚህ ነፋስ ምክንያት ከቤቱ እንዳንለይ ልንለምነው ያሻል። ... እንዲህ ካልሆነ እና በወቅታዊ ችግር በሚነሳ ሽብርና ሁከት ፣ ስሜታዊነት በሚወልደው ወኔ እና እልህ መፍትሔ ለማግኘት ብንወጣ ብዙ ጥፋትን እናጠፋለን ... በርግጥ መፍትሔ የሚሰጥ እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ቢሆንም ፤ እኛ እና እርሱ አባት እና ልጅ እስካልሆንን ድረስ ሐዋርያው " ...በእምነት ስላልተዋሃደ ... አልጠቀማቸውም " እንዳለ አንጠቀምም።

እናም ወንድሞቼ ሆይ ወደ መልካሙ ጎዳና እንመለስ ፤ ዘወትርም በጸሎትና በምልጃ በመንፈስም ወደ አምላካችን እናመልክት ፤ ያኔ ዉሉ የጠፋ እስኪመስል የተተበተበው ቋጠሮ ይፈታል ... ችግር ከስሩ ይነቀላል !!!

እንግዲህ በቀረውስ ፤ ወንድሞች ሆይ ፦ ደህና ሁኑ ፤ ፍፁማን ሁኑ ፤ በሰላምም ኑሩ ፤ የፍቅር ፣ የሰላምም አምላክ ከናንተ ጋር ይሁን።

አሜን።

 




14/12/2002
Tromso,Norway

No comments:

Post a Comment