መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Tuesday, February 7, 2012

እውን አንተን ወለደ!?


እውን አንተን ወለደ!?

ለተረት ተረትህ ድርጎ መሞገትን ባትወድም

እኔ ከአንተ መልስ እሻለሁ መቸም ላንተ ወሬ አይገድም
አስጠብቦ አያስጨንቅም
ከጀርባ ላብ አያፈልቅም

መልስ ቢጠየፍ ህሊናህ ፌዘኝነትን ወዶ
ከአባትህ የስልጣኔ ሀሁ አቡጊዳህ ተወላግዶ
ከልጅህ ማነን? ጥያቄ ምላሽህ ተካክዶ
ቢሆንም ያለኽው ቅሉ ያባትክን አጽም አስታመህ
ባባትህ ብርሃን ጨልመህ
በስልጣኔው ሰይጥነህ
ቢሆንም ያለኸው ቅሉ
አበው መጠየቅ አይከብድም አሉ
እስቲ ልጠይቅህ ያንተ ማነው አባትህ?

 ያ ስልጣኔንን ቀድሞ የማለደ
በማይነቅዝ ግዙፍ ግብሩ አዲስ ብርሃን የቀደደ
ያ ባየር በረህ የምታየውን ታምር
ባልተጸነሰ ቴክኖሎጅ የማይጠፋ ቅርስ ያኖረ
ያ የላሊበላን መቅደስ ፈልፋይ የአክሱምን ሀውልት ጠራቢ
የጣናን ደብሮች ደባሪ የፋሲልን ግንብ ገንቢ
ያ ስልጣኔን ቀድሞ የማለደ
እውን አንተን ወለደ!?


አባትህ
የዘመን እጣ ድርሻውን ከህይወቱ ተጣጥሎ
ከእውቀት አድማሱ ባሻገር ለግብሩ ካስማ ቸክሎ
ባድማሱ ውስጥ አሸልቦ ካድማስ ማዶ እያለመ
በህሊናው ቋት መዝኖ አድቅቆ እያለመ
አዲስነት እንዳጓጓው
ስልጣኔ እንዳተባው
የዘመንን ፈተና ጥሎ ጭላንጭል እንዳጮለቀ
እንደ ዳመና ግላጭ ስጥ እርካታ እንደናፈቀ
በነገ ብርሃን ድምቀት በተስፋ እንደታረቀ
አንተን ልጁን አፈራ ለእርሱም ለሀገሩም ግራ

አባትህ
እኔ ከሞትኩን ሳይተርት ከቡሊት ጋር አብሮ
የማይሞከረውን ሞክሮ
የማይደፈረውን ደፍሮ
ሁዋላ ቀር ብትለውም ህሊናውን አስጠብቦ
ተአምር ብትለውም ያቆየውን ዘግቦ
ለራሱ ሳይሆን ለሀገር አስቦ
እንዳንተ ጥያቄ ሳይፈራ እራሱን እየጠየቀ
ልራቀቅ ብለህ ብትርቀውም
አሮጌ ብለህ ብትንቀውም
በብራና እየከተበ
ታሪክ እየዘገበ
አለት እየፈረፈረ ድንጋይ እየጠረበ
ያቆየውን ታሪክ ታምር ባይ እውን አንተን ፈጠረ!?

ያ አባትህ ስልጣኔን ቀድሞ የማለደ
ማን ይሙት አንተን ወለደ!?
«አባቴ ይሙት» እንዳትለኝ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ
ትጉህ ወራሽ በማጣቱ
ቦዩ በመገደቡ ጉዞው በመገታቱ
የእሱ እረፍት ሞት አይደለም አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ

መቼም መጠየቅ ሞትህ ነው ድካሙን አትመርምረው
የላሊበላን ድንጋይ እንዴት እንደቦረቦረው
የአክሱምን ግግር አለት እንዴት እንደጠረበው
የዝዋይን የጣናን ደብር እንዴት እንደደበረው
ድካሙን አትመርምረው

ደገፍ ብለህ ፎቶ ተነስ ግርግዳህ ላይ ስቀለው
አየሁት ብለህ ታወራለህ በቪዲዮ ቅረፀው
ላንተ የሚበጅህ ያ ነው
እንዴት ሰራው ካልክማ በጥያቄ ከተጠበብክ
አሰራሩን ካሰላሰልክ በህሊናህ ተወለጀልክ
እኔስ ምን ሰራሁ ካልክማ
ከህሊናህም አትስማማ
ታምር ነው! ካልክ ይበቃል
ማን ባርምሞ ይታዘብሃል አባትህ እንደሁ ሞቷል

አድጎ ባምሳልህ እስክትቃኘው ልጅህ እንኳን ቢጠይቅህ
ላሊበላ በምን ተሰራ? አክሱም እንዴት ቆመ? ቢልህ
በቅሎ ነው ብለህ ንገረው መሬት ፈንቅሎ ወጥቶ
ታምር ነው ይበል እሱም በታምራትህ ተቃኝቶ

አባትህ
ታምር ነው ስትል በሰማህ ያላሰበውን ሰጥተህ
በስንፍናህ አገዛዝፈህ
ከመላእክት ተርታ ስታስገባው ምድራዊ ጥረቱን ክደህ
እንዲህ ሳትሞት ሞተህ
ቢያይህ …
ለሱ ታምር ያ ነው ያልዘራህ አንተ መብቀልህ
ለሱ ያ ነው መርገምቱ
ቢሞትም ዳግማዊ ሞቱ

አባትህ
ምላሱን በጥርሱ ነክሶ በግብሩ በተናገረ
የሀገሩን የኪዳን ቃል ባህር ተሻግሮ ባስተማረ
የዜግነት ውግዘት ሳይነካው ሀገር ምስጢርዋ ገኖበት
ሰንደቅ ግርማዋ ደምቆበት
የኖረበትን ዘመን በግብሩ ስንዝር እየለካ
ኋላቀር የምትለውን እውን አንተን ይተካ!?
«አባቴ ይሙት» እንዳትለኝ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ
ትጉህ ወራሽ በማጣቱ
ቦዩ በመገደቡ ጉዞው በመገታቱ

ጉድና ጅራት ኋላ ነው አንተም ያባትህ ጉድ ነህና
ተረት ተረት ቁጭ በልና …
«ሮሀ በሚባል መንደር በተራራ በታጠረ
አንድ ንጉስ ነበረ …
ከእናቱ ማህጸን ሲወጣ ገና ከመወለዱ
በንቦች የተተለመ የወደፊት መንገዱ
የአምላክ የእውነት ቃሉ ትንቢት አይቀርምና
አድጎ ዙፋኑን ጫነ በረከቱን ተቀባና
ከዚያማ ምኑ ቅጡ! እግዜር እጁን ጫነበት
ብርሃኑን አካፈለው መንፈስቅዱስ እፍፍፍ አለበት
በብርሃን አምድ አመልክቶ ብርታቱን ሰጠውና
ቤተመቅደስ እንዲያንጽ ሃይማኖቱን እንዲያቀና
ለይስሙላ እጁን ሲያነሳ መላእክት ተረባርበው
የማይቻለውን ችለው
ይኸውልህ ይህን ሰሩ በሱ አካል እነሱ አድረው»
እያልክ ለልጅህ ተርተው
ያምላክ ትንግርት አድርገህ
ያባትክን ድካም ክደህ

ያኔ ህሊናህ ይጃጃላል ቆስሎ … መግሎ … አይጠነባ
በባዶ ሞራህ ተሸብልሎ ከከርስህ ውስጥ ነው ‘ሚገባ

አባትህ
ጊዜውን በሰዓት ሳይሆን በስራው ፍሬ እየለካ
ድካሙን ትንግርት ባይ እውን አንተን ይተካ!?
ያ የላሊበላን መቅደስ ፈልፋይ የአክሱምን ሀውልት ጠራቢ
የጣናን ደብሮች ደባሪ የሐረርን ግንብ ገንቢ
ያ ስልጣኔን ቀድሞ የማለደ
የዘላለም ቅርሱን ተራች እውን አንተን ወለደ!?
እውን አንተን ወለደ!?
ትንግርት ነን


በድሉ ዋቅጅራ (ፍካት ናፋቂዎች, 1999 ዓ.ም.)

No comments:

Post a Comment