መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Saturday, December 11, 2010

ያማል!

ያማል!

እና እንደነገርኩሽ ...
የሚወዱትን ሰው ቀጥሮ እንደመጠበቅ
የነፍሰ-ጡርን ሞት አይቶ እንደመሳቀቅ
ባልታሰበ ናዳ ተመትቶ እንደመድቀቅ
ከተስፋ ጉልላት ተገፍቶ እንደመውደቅ
ታምር በበዛባት በዚች ቧልተኛ ዓለም
ከዚህ የበለጠ ምንም ሕመም የለም።
***
አውቶቡሱ ያማል
ሚኒባሱ ያማል
ላዳ ታክሲው ያማል
የማይጎድል የሰው ጎርፍ ... ደራሽ ማዕበሉ
         ... የዕንባ ቅጥልጥሉ
ምን ብዬ ልንገርሽ ... ያማል ይኼ ሁሉ።
***
እና እንደነገርኩሽ ...
የሚወዱትን ሰው ቀጥረው ካረፈደ
የሚያፈቅሩትን ሰው ቀጥረው ካረፈደ
ነገር ተበላሸ ሕመም ተወለደ ጨጓራ በገነ
እሳት በእንፋሎት መልክ በ'እህታ' ተነነ
የሚሆነው ሳይሆን የማይሆነው ሆነ
ሁሉ ተቀይሮ ተተካ በሲቃ
ምን ብዬ ልንገርሽ ይህም ያማል በቃ።
ወጭ ተራማጁ አስመሳይ ሰጋጁ
ፀሐዩ ዝናቡ ... የ'ለምን' ምክንያት የ'ለምን'ሰበቡ
ተቆራጭ አበባ ሊቆረጥ ማበቡ ... ውል የለሽ ደመና ተራራን መክበቡ
እልፍ አእላፍ ኮከብ ጨረቃን ማጀቡ
ደግሞ ለ'ርሷ ግጥም 'እናቷን' ጨረቃ
ምን ብዬ ልንገርሽ ይህም ያማል በቃ።
***
እና እንደነገርኩሽ ...
ጉንጭ የማትሞላ ኬክ አስር ብር የሸጠ
የካፌ አሳላፊ ወደ'ኔ አፈጠጠ
ዘይት የነካውን መንታ እጁን አጣምሮ
ምን ልታዘዝ ይላል ቁልቁል አቀርቅሮ
'ምን ልታዘዝ?' ይላል 
እንዴት ቅጥሉ ሰው ቅጥሉን ሰው ያዛል?
ማኪያቶ ልዘዝ? ... ካፑችኖ ልዘዝ? ... ጥቁር ቡና ልዘዝ
ለምን ሰው አላዝም?  ... መታዘዝ መናዘዝ እርግማን የሆነው 
ካፌውን ሲያሳልፍ ... እራሱ ግን የሚያልፍ
ቁልቁል አቀርቅሮ ... ሞቱን ባንገት ቀብሮ
'ምን ልታዘዝ?' ይላል ... 
አንድ ማኪያቶ ካንድ እሷ ጋር ልበል
አንድ ካፑቹኖ ካንድ እሷ ጋር ልበል?
ከጥቁር ቡና ጋር እርሷን አምጣ ልበል?
ተይ አታስለፍልፊኝ ይኼ ሁሉ ያማል
የላስቲክ አበባ የአርቲቡርቲ ስዕል
የጭቃ እሾህ ወግቶት እዥ ያወጣ ቁስል
ትልቁ ነቀዝ ሰው የማንቀዙን ያህል
ብዙ አታስለፍልፊኝ ...ይኼ ሁሉ ያማል።
***
እና እንደነገርኩሽ ...
ላንች የያዝኩት አበባ ... መጠውለግ አመጣ
ፀሐይ ገባ ወጣ ... ዝናብ ቀረት መጣ
ጨረቃ የለችም ... 'እናቷን' ስላልኳት?
ደግሜ ሰድቤ ሺ ዓመት እንዳይገርማት
'እ-ና-ቷ-ን! እናቷን ጨረቃ ... ተይ አታስለፍልፊኝ ይህም ያማል በቃ።
***
ግን ... እኔ አንችን ስወድሽ
እኔ አንችን ስወድሽ ይኼን ሁሉ ችዬ ... ነው የምጠብቅሽ
ቢሆንም ግን ያማል!!!

የሴት ደራሲያን ማኅበር
በያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት አዘጋጅቶት በነበረ የጥበብ ዝግጅት ላይ የቀረበ

No comments:

Post a Comment