መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Tuesday, June 29, 2010

እኔ እና ወንድሜ

እኔ እና ወንድሜ

የአባቴ እና የአባቱ
የጥንስሳቸው መሰረቱ
ሐረጋቸው ሲመነዘር
አንድ ተብሎ ሲቆጠር
ሀሳባቸውና ፈቃዳቸው
የአኗኗር ቅኝታቸው
ለየቅል የተገነባ
ላይገናኝ ቃል የተጋባ

ነበሩ...አሉ ሁለቱም
የተራራቁ በጣሙን

ወንዘኞችና ጎጠኞች
ለብቻየ የሚሉ ምቀኞች
ልዩነትን እንደ ልዩነት
ያልታደሉ ለመመልከት
ያልነበረውን አንድነት
ያልነበረውን ሕብረት
እንደነበረ የሰበኩ

ነበሩ...ይላሉ የታዘቡ
የትዝብት መጽሐፋቸውን ሲያነቡ

ታዲያ...የአያቴ እና አያቱ
ሆኖ ውርስ ለአባቴ እና ለአባቱ
ሀሳብ ለበላት እማማችን
ኑሮ ላደከማት እናታችን
ሌላ ሰቀቀን ሆነባት
የማይሽር የጎን ውጋት

የኔ እና የወንድሜ እማማ
የማይቻለውን ችላ ተቀምጣ
ውጋቷን እያስታመመች አዘዘችን
የአባቶቻችሁን ቁርሾ እርሱት አለችን።

እኔ እና ወንድሜ በፋንታችን
የእምዬን መልዕክት አሽቀንጥረን
ላንተማመን ቃል ገባንላት
የአባቴን እና የአባቱን ጎጠኝነት
በዘመነ ስልት አዜምንላት

አሁንም እናታቸችን ትጮሃለች
በደከመ ድምፅ ታቃትታለች
ባባቶቻችሁ ደም መቃባት
አንድ ላትሆኑ መለያየት
አቁሙ!!! በቃችሁ ትለናለች።

አሁንም ደግማ ደጋግማ
እራሷን ደጋግፋ ቆማ

" አባቶቻችን ለራሳቸው
በራሳቸው መንገድ ሄደው
ይሆናል...የማይሆነውን አድርገው።
እኛ በ'ነርሱ ቅዠት
ዳግም ላንጓዝ ወደ ጥፋት
በ'ናታችን ፊት ቃል ገባን
ብላችሁ በይፋ ተማማልን
ህመሜን ውጋቴን ተረዱልኝ
መሳቀቅሽ ይብቃ በሉኝ
ያኔ...
ያኔ ውጋቴን እረሳለሁ
ስለፍቅር እና ሰላማችሁ
አብሬያችሁ እዘምራለሁ "

እያለች...
አምርራ ትነግረናለች።

ታዲያ...እኔ እና ወንድሜ አሁን
በራስ ፈቃድ መጓዝን
መደማማቱን ትተን
ብንሰማት እናታችንን
የቀደመውን የኃጢአት ውል
ጃ...ይሰርያል።

በመጨረሻው እኔ ገባኝ
የእናቴ ጥሪ ተሰማኝ
ወንድሜስ? ይሰማው ይሆን? ? ?
በተሰማው...


አቤሎ እና እኔ እንዳሰብነው

እኔ እንደጻፍኩት
20/09/97
ዲላ

No comments:

Post a Comment