መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Thursday, August 5, 2010

ሊያሳስበን የሚገባ ሌላ ጉዳይ ...


በስመ ሥላሴ አሜን።
የቤታችንን ችግር አስመልክቶ  የተለያዩ ነገሮችን  በተለያየ መንገድ  ከተቆርቃሪዎችም ሆነ ግድ ከሌላቸው ወገኖች ብዙ ሰምተናል ... ከአንዳንዶቹም ጋር አብረን መክረናል ... ችግር ፈጠሩ ያልናቸውን አካላትንም  ኮንነናል ፤ ወቅሰናል ... መፍትሔ ስለምንለውም ነገር ብዙ ብለናል ... ነገር ግን አሁን በፊታችን ተገልጦ የምንጯጯህበት ይህ የቤተ-ክህነት ችግር እኛ ባሰብነውም ይሁን በሌላ ዘዴ ቢፈታ ወይም የተፈታ ቢመስል  እንኳ ትቶት ሊያልፈው ስለተዘጋጀው ጠባሳ ስንቶቻችን እናውቃለን?
በምንኖርባት በዚች አለም መሪዎች በተመሪዎች ላይ ቀንበር ሲያከብዱ ፤ ግፍን ሲያደርጉ ተመሪዎቹ በመሪዎቹ ላይ መነሳታቸው ፤ በተወሰኑትም መስዋዕትነት ሌሎቹ ነፃነታቸውን እንደሚያገኙ ታሪክ ምስክር ይሆናል ፤ ... ነገር ግን ይህን መሰሉ ክስተት የሚሰራው በአለም ነው! ... ምንም እንኳ እኛ ምዕመናን በአለም ውስጥ የምንኖር ቢሆንም ... በእግዚአብሔር ቤት አካሔዱ የተለየ ነው ... ሊለይም ይገባዋል ... ምክንያቱም አልቻለን እያለ ቢቸግረን ነው እንጅ ልንፈጽመው የምንወደው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ነውና ... ሀገራችንም በሰማይ ነውና ... በመሆኑም የቤተ-ክህነት ችግር መፍትሔ በምስኪን ምዕመናን መስዋዕትነት ወይም ዋጋ ሊታሰብ አይገባውም  ... ለዚያውም መስዋዕት ስለሆኑበት ነገር በውል በማይረዱበት ሁኔታ ...
በየገጠሩ በስሚ ስሚ ፤ በየክፍላተሃገራቱ ካልተጣራ የወሬ ምንጭ ከሰሙት የተነሳ የሚስቱትን ወገኖቻችንን እንኳ ትተን በአዲስ አበባ ለቤተ-ክህነቱ ቀረብን ፤ ነገሩንም ከተለያዩ ምንጮች ሰማን  የምንል ሰዎች የምንሰጣቸውን አስተያየቶች ለአፍታ ብንመለከት ከቤተ-ክህነቱ ችግር ባልተናነሰ ልንነጋገርበት ፤ መፍትሔ ልናፈላልግበት የሚገባ ጉዳይ እንዳለን ማስተዋል አይቸግርም። እንደ ሕዝብ፦  ችግሮችን በቀና መንፈስ የምንረዳበት ፤ ከአሉባልታ በፀዳ መልኩ ለመፍትሔ የምንረባረብበት ፤ መፍትሔን ለመፈለግ በሚደረግ ሂደት የሚመጣን ማንኛውንም በጎ እና ክፉ ነገር በኃላፊነት በፀጋ የምንቀበልበት ልማድ እንደሌለን ... ከዚህ በተጨማሪም ክርስቲያኑ ምዕመን በመንፈሳዊ ደረጃው እና ብርታቱ አንዱ ከሌላው እንደሚለያይ ይታወቃል ... በመሆኑም ምስኪኑ ምዕመን ከሚያየው ነገር የሚስተው ይበቃዋልና ... ምንም ያህል እንኳ የቤተ-ክህነቱን ችግር ያወቅን ፤ የጠነቀቅን ቢመስለን፦ የምናደርጋቸው ፤ የምንናገራቸው ፣ እና የምንፅፋቸው ነገሮች ሌሎችን እንዳያስቱ ፤ ልንጠነቀቅ ይገባናል ... እኛ እግዜር እድሜ ለንስሃ ከሰጠን ፤ መሳታችንን በተረዳንና በገባን ጊዜ ልንመለስ እንችላለንና ... ስለእውነት ለመነጋገር ስንቶቻችን ካየነው ፣ ከሰማነውና ፣ ካነበብነው የተነሳ የእግዚአብሔርን የቸርነት ስራ ተጠራጥረናል? ... ስንቶቻችን ስለመንፈሳዊ ሕይወት ያለን ግንዛቤ ተዛብቶብናል? ... ስንቶቻችን መልካሞቹን አባቶቻችንንና መምህራኖቻችንን ከክፉዎቹ ጋር ጨፍልቀን የማይገባውን ተናግረናቸዋል? ... ስንቶቻችን ወደቤተ-እግዚአብሔር ለመሔድ አፍረናል? ... እኛ ስለራሳችን መልካምን ልንል እንችላለን ... ነገር ግን ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ያያል ... ስለራሳችን እንዲህ ካሰብን ደግሞ ... በእምነት ከእኛ ስለሚደክሙ ... እግዚአብሔር ግን አጥብቆ ስለሚሻቸው ... ስለነርሱ ደግሞ ልናስብ ያስፈልገናል ... ስንቶቹ ይሆኑ ለንስሃ አባቶቻቸው ያላቸው ፍቅር የሚቀንሰው? ... ስንቶቹ ይሆኑ ለድካማቸው ምክንያት ይህንን ነገር የሚያደርጉት? ...

በርግጥ፦ ምዕመናን በሌሎች ሰዎች አስተሳሰብና አካሔድ እየተነዱ ከመንገድ ከመውጣት ፤ በጎ እና ክፉን በራሳቸው ህሊና ሊመረምሩ ፤ በጎውንም ሊከተሉ ይገባቸዋል። .... እንዲያም እንኳ ቢሆን እግዚአብሔር መምህራንን ማስቀመጡ እንዲህ ለሚደክሙት መንገድን ይመሯቸው ዘንድ ነውና የመምህራንን ፍለጋ መከተል እንግዳ ነገር አይደለም ... በመሆኑም የሚከተሉ የሚከተሉትን መመርመር እንዳለባቸው ሁሉ  ... የሚከተል ያላቸውም ለሚከተላቸው የማይገባ መንገድን ማሳየት የለባቸውም ... ምክንያቱም ይህ ክርስትና ነውና!!! ... በክርስትና ደግሞ ሁለቱም ወገኖች ይመረመራሉ ... ከስራቸው የተነሳ ይፈረድባቸዋልም ... አንዱም ስለሌላው ይጠየቃል። ... ይህም ማለት እኛ የምንናገራቸውና የምንፅፋቸው ሌሎችን  ከእግዚአብሔር መንገድ የሚያወጡ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርብናል ... የምናደርጋቸው ፣ የምንናገራቸውና ፣ የምንፅፋቸው ነገሮች የፈለገውን ያህል ሰላም የሚያመጡ  ቢሆኑ ... የቱንም ያህል አስተማማኝ መፍትሔ ቢይዙ ... የተወሰኑ ምዕመናንን የሚያጠፉ ስላለመሆናቸው እርግጠኞች ልንሆን ያስፈልገናል ... ምክንየቱም የአምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ሁሉ በሰላም በእቅፉ ውስጥ ይሆኑ ዘንድ እንጅ አንድስ እንኳ እንዲጠፋ አይደለምና .. 
ይህም ሲባል ስለመፍትሔው መነጋገሩንና  መወያየቱን አንዳች የማይገባ ነገር ለማድረግ አይደለም ... እንዲያውም ይህ የመላው ምዕመናን የውዴታ ግዴታ ነው  ... እንዲህ ማለቴ ... በዚህ ችግር ውስጥ የመፍትሔ አካል ለመሆን ከታሰበ  እያንዳንዱ የቤተክርስቲያኒቷ ልጅ የራሱን ድርሻ ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባዋል ለማለት እንጅ ... እንዲህ ካልሆነ ሁሉም ነገር ለሁሉም በመሰለ ሁኔታ እየተነገረ ያለ የመፍትሔ ሀሳብ መፍትሔ አቅራቢውንም ፣ ምዕመናኑንም ፣ ቤተክርስቲያኒቱንም አይጠቅምም!!! ... አንዱን ለማልማት ሌላውን ቢጎዳ ነው እንጅ ...  እንደ ካህን ምን ይጠበቅብኛል? ... እንደ ሰበካጉባኤ አባልነቴ ምን ይጠበቅብኛል? ... እንደ መምህርስ? ... እንደዘማሪስ? ... ያልን እንደሆነ እና ያንኑ የድርሻችንን ከተወጣን ግን በቂ ነው። ... ምንም ቢሆን  ቤቱ የእግዚአብሔር ቤት ነውና ...  
በቀረውስ፦ ምንም በጫና ውስጥ ብንሆን ፤ ምንም የምናየውና የምንሰማው እምነታችንን የሚፈታተን ቢሆን ፤ እግዜር የማይወደውን ከማድረግ እንቆጠብ ... በሃይማኖታችን አስተምህሮ ለትዕግስት ወሰን የለውምና ... እንታገስ ... ክፉን ከማድረግ እንታገስ ... መልካምን ብቻ እያደረግን የአምላካችንን የምህረት ስራ እንጠብቅ ... ከዚህም ጋራ ለራሳችን፦ “ በመከራችን ጊዜ እግዚአብሔር የትዕግስትን ፍፃሜ ይሰጠን ዘንድ ስለነፍሳችን ትዕግስት እንማልዳለን “ እንበል ... ስለአባቶቻችንም ደግሞ፦ “ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እነሱ ናቸውና እግዚአብሔር እነሱን ለረጂም ወራት ይሰጠን ዘንድ ያለ ነውር በንፅህና ሁነው በዕውቀት የሃይማኖትን ቃል ያቀኑ ዘንድ ስለ ጳጳሳቶቻችን እንማልዳለን “ እንበል።
የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይቅረበን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።  
 29/12/2002 
Tromso, Norway

No comments:

Post a Comment