የፈጣሪን መኖር እንዴት ማወቅ ይቻላል?
ሰው በልዩ ልዩ ተፅዕኖ ምክንያት በራሱ ፈቃድና ውሳኔ ካልተወው በቀር ፤ የፈጣሪን ሀልዎት ( መኖር ) ፈልጎና መርምሮ የሚያውቅበት እውቀትና ችሎታ ፤ ደግና ክፉን ለመለየት የሚያስችለው ሕገ - ልቦና ( የሞራል ሕግ ) በተፈጥሮ እንደተሰጠው የታመነ ነው። በሞራል ሕግ - በምርምር የፈጣሪን መኖር ማወቅ አይቻልም በማለት በነፃ ፈቃዳቸው በድፍረት ወስነው የሃይማኖትን ነገር ፈፅሞ እንዳያስቡ የኅሊናቸውን በር የዘጉትን ሰዎች ወደጎን ትተን ፤ በመጀመሪያ ሥነ-ፍጥረትን ቀጥሎም ሰብአዊውን ፍጡር ፤ ሰውን ፦ በተለየ መልኩ በመመርመር እንዴት የፈጣሪን ሀልወት ማወቅና ፤ መረዳት እንደሚቻል እነሆ ፦
የሥነ-ፍጥረትን ገጽታና ሁኔታ ፤ አሰራርና አካሄድ በመመልከት የማያደንቅ ሰብአዊ ፍጡር አይኖርም። በአጠቃላይ የሥነ-ፍጥረትን ውበት ፣ የአፈጣጠሩን ሥርዓት ፣ በቀን የፀሐይ ብርሃንና ሙቀት፣ በሌሊት የጨረቃዋን ድምቀት ፀጥታና ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ በተረጋጋ ኅሊና ለሚያስተውለው ሁሉ የመገረም ስሜት ያድርበታል። ከበላያችን ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የተዘረጋው መጨረሻ የሌለው የሰማዩ ስፋትና ጥልቀት ፤ በሌሊት የሚያብረቀርቁት ከዋክብት ብዛት ፤ የአቀማመጣቸውና የእንቅስቃሴያቸው ሥርዓት ፣ የዘመናት መፈራረቅና ሌሎችም የተፈጥሮ ክስተቶች እጅግ ያስደንቃሉ። በተለይም በምድራችን ዙሪያ የሚገኙት ሕይወት ያላቸው ለምለም እፅዋት ፣ በእግር የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ፣ በክንፍ የሚበሩ አእዋፍና የሌሎችም አፈጣጠር በየወገናቸው ሲጠና ይልቁንም የሰዎች ልጆች ረቂቅ ተፈጥሮ ሲታይ በአጠቃላይ የሥነ-ሕይወት ክስተት ጉዳይ ሲመረመር አስተዋይ ኅሊና ያለውን ሁሉ ያስጨንቃል ፤ ያስጠብባል።
የተፈጥሮን እንቆቅልሽ ፤ የሕይወትን ትርጉም ለማወቅና ለመመርመር የዚህ ዓለም ሊቃውንት ብዙ ጥረት አድርገዋል ፤ በዚህም የዚህ ዓለም አፈጣጠርና አካሄድ በሥነ-ሥርዓት ታስቦና ተሰልቶ በረቀቀ ቀመር የተሰናዳና የተዘጋጀ መሆኑን የተረዱ ፈላስፎች ይኽን ሁሉ ያደረገ ወይም የፈጠረ ፤ ከፍተኛ ማስተዋልና ጥበብ ያለው አንድ ኃይል መኖር እንዳለበት ያምናሉ። እንደነሱ አስተያየት የአንድ ነገር መኖር ፤ የአንድ ሁኔታ መከሰት ፤ የአንድ ነገር መፈፀም ( effect ) እንዲሁ ያለ ምክንያት ፤ በአጋጣሚ ወይም በዕድል የሚሆን ነገር እንዳልሆነና ለሁሉም ነገር መነሻ ምክንያት ማለት መንስኤ ( cause ) እንዳለው ያምናሉ።
የሰው ልጅ ችሎታው እስከፈቀደለት ድረስ የእውቀቱን አድማስ እያሰፋ በመሄድ የምርምሩ ኢላማ የሆነውን ሥነ-ፍጥረትን ከመመራመር አላቋረጠም። ምክንያትን በምክንያት እያፈላለገ መላምትንና ግምትን በማስረጃ እያመሳከረ ፤ የዓለምን ጥንተ ተፈጥሮ ፣ የሕይወትን ዓላማ ፣ መነሻና መድረሻ ሌሎችንም ተመሳሳይ ነገሮች ለማወቅ ይጥራል። በዚህና በመሳሰለው መንገድ አሳቡን እያራዘመ ምክንያቱን እየደረደረ ርቆ በእግረ ልቦና በመሄድ ወደ መጀመሪያው መንስኤ - ቀዳማዊው ምክንያት ( prime cause ) ይደርሳል። በዚህ የአእምሮ አስተሳሰብ ሥርዓትና ሂደት መሰረት ፤ አንድ አይነት እንቅስቃሴን ብንመለከት ከኋላው የሚያንቀሳቅሰው ኃይል አለ። ለምሳሌ ዛፎች የሚንቀሳቀሱት በራሳቸው የውስጥ ኃይል ሳይሆን ከውጭ በመጣ ነፋስ እንደሆነ የታወቀ ነው። የነፋሱ እንቅስቃሴ ደግሞ ሌላ መንስኤ አለው። በምሳሌው እንደተገለጸው ሳይሆን ፤ በተፈጥሮ ሂደት ሌላ ዓይነት የረቀቀ የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ አለ። ይህና የመሳሰሉት የሥነ-ፍጥረት እንቅስቃሴዎች ሁሉ የቅርብና የሩቅ አንቀሳቃሽ ከበስተኋላቸው ይገኛል። እንግዲህ አንዱ ለሌላው ፤ ሌላውም ለሌላው የእንቅስቃሴ ምክንያት እየሆነ ይሄድና በማብቂያው ላይ ምንም አንቀሳቃሽ ወደሌለው የመጀመሪያው ወሳኝ አንቀሳቃሽ ኃይል ( unmoved mover ) በፍኖተ አእምሮ መድረስ ይቻላል። በዚህም ብዙዎች ከቅርቡ ወደሩቁ ፣ ከአሁኑ ኑሮ ወደ ጥንተ ተፈጥሮ በመሸጋር ፤ የአስገኝን አስገኝ ፍለጋ በመከተል የጊዜን ርዝመት አልፈው ፤ ከቀዳማዊው ዓረፍተ-ዘመን ሲደርሱና መገኛውና ምንጩ የማይታወቅ ፤ አስገኝ የሌለው ( ለህላዌው አመክንዮ ምክንያት የሌለው ) ፍፁም ጥበብና እውቀት ያለው አንድ ምሥጢራዊ ኃይል መኖሩን በማመን ሀልወተ እግዚአብሔርን - እግዚአብሔር መኖሩን ለማወቅ ችለዋል።
" እንስሶችን ጠይቅ ያስተምሩህማል ፤ የሰማይ ወፎችን ጠይቅ ይነግሩህማል ፤ ወይም ለምድር ተናገር ፦ እርሷም ታስተምርሃለች ፣ የባህር ዓሳዎች ይነግሩሃል ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ፤ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው? " ኢዮብ 12 ፦ 7-9
ሥነ-ፍጥረትን መነሻ በማድረግ የፈጣሪን መኖር ወደማወቅ እንደምንደርስ ሁሉ ፤ ምንም እንኳ የሥነ-ፍጥረት አንድ አካል ቢሆን ቅሉ ከተለየ የተፈጥሮ ባህሪው የተነሳ ፤ የሰውን ልጅ ፦ የተፈጥሮ ባህሪዩን ምንነነት ፣ ይልቁንም የህልውናውን ጥንት እና ፍፃሜ ፣ በተለይም የነፍሱን ነገር በመመርመር ፤ እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እንደርሳለን። በአሁኑ ጊዜ ፦ ሰው ከራሱ ውጭ የቅርብና የሩቅ አካባቢውን ከመቼውም በበለጠ በሰፊው በማጥናት ላይ ቢገኝም ፤ ስለ ሥነ-ልቦና እና ነገረ-ነፍስ እስካሁን የተደረጉት ጥናቶች ጠቃሚ ምልክቶች ቢታዩባቸውም ውጤታቸው ግና እምብዛም የሚያረካ ሆኖ አልተገኘም (1)። ( " Psychology, albeit [ though ] with marked lack of success, seeks to describe the constituents and workings of the human mind " )
የሰው ልጅ የራሱን ህላዌና ውሳጣዊ ባህርዩን ሲመረምር ከግዑዙ ከግሡሡ ( ከሚዳሰሰው ) ቁስ አካላዊ ክልል የወጣና የተለየ ፍጡር መሆኑን ያስተውላል። እርግጥ ነው ፤ ሰው ፦ በዚህ ዓለም ውስጥ ከሚገኙትና በተለምዶ አባባል ከአራቱ ባህርያት የተፈጠረና የእነርሱም ተረጅና ተጠቃሚ ቢሆንም ከእነርሱ የበላይነት ችሎታ ስላለው ተፈጥሮን እየተቆጣጠረ ለአገልግሎት እንዳዋላቸው እናያለን። ታዲያ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ፤ ይህ የገዥነት ችሎታ ከየት መጣ? የሚለው ብቻ ሳይሆን ፤ ይህ " ሰው " እየተባለ የሚጠራው ባለ አእምሮ ፍጡር ከዚህ ዓለም ጥንተ ነገሮች ( elements ) ብቻ የተገነባ የቁስ አካል ውጤት ነውን? የሚለውም ጭምር ነው። የሰው ልጅ ፦ ስብዕናው ማለት እኔነቱ ፣ አእምሮውና ልቦናው ፣ ሰብአዊነቱና ፍቅሩ ፣ ስሜቱና ሌሎቹም መንፈሳዊ ጠባይዓቱ እንደቁስ አካል ተፈጥሮ ፤ ክብደታቸው ስንት እንደሆነ በሚዛን ተመዝኖ ፣ ጎናቸውና ቁመታቸው በክንድ ተለክቶ ፣ ቅርጻቸውና መልካቸው በስዕልና በቀለም ተገልጾ ፤ በቤተ-ሙከራ ገብቶ በልዩ ልዩ መሣሪያዎች ተመርምሮ ሊታወቅ አይችልም። ስለዚህ ሰውን ሰው ከሚያደርጉት የተለዩ ጠባይዓቱ ከግዑዙ ከግሡሡ ማለት ከሚታዩት እና ከሚዳሰሱት የተገኙ ነገሮች እንዳልሆኑ ያመለክቱናል። እንዲህም ስለሆነ፦ ከሥጋ ባህርይ የተለየች ፤ መንፈሳዊ ህላዌ ያላት ባለ አእምሮ ፤ ጥበብና ማስተዋልን የተጎናጸፈች " ነፍስ " ተብላ የምትጠራው በሰው ተፈጥሮ ውስጥ እንዳለች እንገነዘባለን።
አንድ ነገር መሰሉን ( ዘሩን ) ያስገኛል እንጅ ከባህረዩ ውጭ የሆኑትን ነገሮች ሊያመነጭ ( ሊፈጥር ) አይቻለውምና ፤ የነፍስ መንፈሳዊ ህላዌና ሉዓላዊ ባህርያት ፤ ማለትም ለባዊነት ( የማሰብ ) ፣ ነባቢነትና ( የመናገር ) ፣ ሕያውነት መገኛ ምንጭ የቁስ አካል ንጥረ ነገሮች ውህደት ውጤት ናቸው ብሎ ማመን እጅግ ያዳግታል። ስለዚህም የእነዚህን ሰብአዊና መንፈሳዊ እሴቶች መንስኤና መገኛ ፤ ከቁስ አካል ተፈጥሮ ማለት ከመሬት ጥንተ ነገሮች ተፈልጎ ከሌለ ፤ ግዴታ ከቁስ አካል ክልል ውጭ ከልዩ ምንጭ መገኘት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም አንድ ነገር ያለ አንዳች ምክንያት ፣ ያለምንም መንስኤ እንዲሁ ወደ መኖር አይመጣምና ነው። ስለዚህ የነፍስን ባህርያት አይነት የመሰሉ መንፈሳዊ ጠባይዓትን ሊያስገኝ የሚችል ፤ ከቁስ አካል ውጭ ፣ ከሥነ-ፍጥረት ሁሉ የላቀ፣ ባህርዩ ረቂቅ አኗኗሩ ምጡቅ የሆነ ታላቅ መንፈሳዊ ኃይል እንዳለና እንደሚኖር በሰው የተለየ ተፈጥሮ ምክንያት የተነሳ ለማመን እንችላለን። ይህም መንፈሳዊ ኃይል ከቁስ አካል የማይገኝ ልዩ ባህርያትን ለነፍስ ያጎናጸፈ ፤ ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረ እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ እናምናለን።
" ፈጣሪ በፍጥረቱ ለፍጥረቱ በግልጥ ይታወቃል " ሮሜ 1 ፦ 19-21
በተጨማሪም ፦ የሰው ልጅ ማድረግ የሚገባውንና የማይገባውን ነገር በትክክል ለይቶና አመዛዝኖ የሚያውቅበትና የሚመራበት የግብረ-ገብ ሕግ በልቦናው ተጽፎ መገኘቱ ሌላው ሀልወተ ፈጣሪን የምንረዳበት መንገድ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፈላስፋው ኢማኑኤል ካንት ስለሃይማኖት እውቀት የሰጠውን ጠቃሚ አስተያየት ጨምረን እንመልከት ፦ አንድ ሰው ማንም ሳያስገድደው ፤ የግል ፍላጎቱን ወደ ጎን ትቶ ፤ በበጎ ፈቃዱ ማድረግ የሚገባውን ነገር ሲያደርግ ( when one does what he ought to do ) የመንፈስ ደስታ ፣ እርካታ ይሰማዋል ፤ የሚገባውን ሳያደርግ ሲቀር ግን ያዝናል ፤ ሕሊናውም ይወቅሰዋል ፤ የቁጭት ስሜትም ያድርበታል። ይህ በሰው ልጅ ባህርይ ብቻ የሚገኘው የሞራል የውዴታ ግዴታ ስሜት ( this sense of " ought " ) ከየት ሊመጣ ይችላል? እንደ እርሱ ( ካንት ) አስተሳሰብ ግብረገባዊ ( ሞራላዊ ) ሁኔታ በሚገጥመን ጊዜ ፤ ለምሳሌ ጥቅም በሌለበትና አስደሳች ባልሆነ ሁኔታ ግዴታችንን ለመወጣት ፈቃዳችን በሚነሳሳበት ጊዜ ቀጥታ ግንኙነት የምናደርገው ፤ ለስሜቶቻችን በሚታወቀውና በሚታየው ፤ ከሞላ ጎደልም በእኛ አሳብ ውስጥ ከተገነባው ዓለም ጋር ሳይሆን ከእኛ ከራሳችን ጥገኛ ካልሆነው ፤ ከእኛ ውጭ ከሚገኘው ራሱ በራሱ ካለው ዓለም ጋር ነው። ይህንንም የግብረ ገባዊነት ( የሞራል ) ዓለም - " እኛ ራሱ አባላት የሆንበት ፤ የቡሩካን መንፈሶች ማህበር ያለበት " በማለት ይጠራዋል (2)። ( " Kant thought of it as a community of blessed spirits of which we ourselves are members ... there is an order of reality other than that of the familiar world; it is an order which contains the values of morality such as right and good, and it is an order of which we, in respect of a certain part of ourselves - namely, our moral wills - are members " ... በሰው ልቦና ውስጥ በሚገኘው የኀሊና ሕግና ፍርድ መነሻነትም ፤ የሰውን ልጅ ፦ ይህን የመሰለውን ባህርይ ሊያላብስ የሚችል ይህ ይሳነዋል የማይባል ፤ ፅድቅንና ርትዕን የሚያደርግ ዳኛ መኖሩን ፤ እርሱም ፈጣሪ ዓለማት የሆነ እግዚአብሔር እንደሆነ እናምናለን።
" ሕግ የሌላቸው አሕዛብስ እንኳ ለራሳቸው ሕግ ይሰራሉ ፤ ራሳቸው ለራሳቸው ሕግን ይደነግጋሉ ፤ በሕጋቸውም
የታዘዘውንም ያደርጋሉ። በልባቸውም የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ ፤ ከሥራቸውም የተነሳ ይታወቃል ፤ ሕሊናቸውም ይመሰክርባቸዋል ፤ ይፈርድባቸዋልም። " ሮሜ 2 ፦ 14-16"
የታዘዘውንም ያደርጋሉ። በልባቸውም የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ ፤ ከሥራቸውም የተነሳ ይታወቃል ፤ ሕሊናቸውም ይመሰክርባቸዋል ፤ ይፈርድባቸዋልም። " ሮሜ 2 ፦ 14-16"
ምንጭ ፦ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ, ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት, ( በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የታተመ, ኢትዮጵያ, 1996 ), p25-36.
(1) C.E.M.Joad, Philosophy, London: English Universities Press LTD ( Teach Yourself Books ), 1960, p17.
(2) C.E.M.Joad, Philosophy, London: English Universities Press LTD ( Teach Yourself Books ), 1960, P66.
No comments:
Post a Comment