መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Monday, August 30, 2010

ወመኑ ዘየኃሥሶ ጥበበ ለዝ ዓለም? 1 ቆሮ 1፦20-23

የዚህን ዓለም ጥበብ የሚሻው ማነው?

በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ የመንግስቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ ከተጠራን ከእኛ ከወንድሞቻችሁና ከእኅቶቻችሁ ፤

የጥበብን ፋና ስለመግዛት ፤ የድንቁርናን ጨለማ ስለማራቅ ፤ ራስን ፣ ቤተሰብንና ሀገርን በእውቀትና በሀብት ስለማሳደግ ምክንያት በየትምህርት ተቋማቱ ሆናችሁ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥም ለምትጠሩ ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ለእናንተ ይሁን።


ወንድሞች ሆይ ፦ እግዚአብሔር አምላክ " ንፍጠር ሰብአ በአርኣያነ ወበአምሳሊነ - ሰውን በአርኣያችንና በአምሳላችን እንፍጠር " ዘፍ 1 ፦26 ብሎ የሰውን ልጅ በፈጠረው ጊዜ ፤ ዐዋቂ እንዳደረገው ፤ በጎውን ከክፉ ፣ ብርሃኑን ከጨለማ ፣ ገደሉን ከሜዳ ፣ የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው ይለይ ዘንድ አእምሮውን ፤ ለብዎውን ' እፍ ' እንዳለበት የተገለጠ ነው። ይህም የሰው ልጅ በጥበብ ለጥበብ የተፈጠረና ያለጥበብ መኖር እንደማይችል የሚያሳይ ነው።

ስለዚህም በክርስቶስ ኢየሱስ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ፤ በሁለት ወገን ፦ በምድራዊ እውቀትና በሰማያዊ ጥበብ ተስላችሁ በመንፈስና በስጋ ፤ በእውቀትም በንግግርም ሁሉ በልጽጋችሁ ከየትምህርት ተቋማቱ የትምህርት ጊዜያችሁን ፈፅማችሁ ስትወጡ በምትደርሱበት አካባቢ ሁሉ ፤ ለወገኖቻችሁ የአምላካችንን የፍቅሩንና የማዳኑን ነገር እንደምትነግሩ ባሰብን ጊዜ ዘወትር ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ፤ ምክንያቱስ ፦ የጥበብ ባለቤት ራሱ አምላካችን በመሆኑ ፤ ሰዎች ጥበብን እንዲያገኙ ፣ በዕውቀት እንዲጎለምሱ ፣ ባወቁትም ወገኖቻቸውን እንዲጠቅሙበት ይፈቅዳልና ነው። ስለሆነም ከፊት ይልቅ አብዝታችሁ ብትተጉ ያለ ነቀፋ እስከመጨረሻው ድረስ አጽንቶ ሊጠብቃችሁ ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር ፍፁም የታመነ ነው።

ወንድሞች ሆይ ፦ መማር መመራመራችሁ ፣ ማወቅና መጠበባችሁ ፣ መላቅና መመንጠቃችሁ ኃጢያት ሳይሆን ለእኛ ለወገኖቻችሁ ከኩራትም በላይ ነበር ፤ ነገር ግን ጥበብ እናውቃለን በማለት በመንፈሳዊ እውቀት ለማደግ ትማሩ ዘንድ እምቢ እንዳላችሁ ፤ እንዳንጎራጎራችሁና ዋዛ ፈዛዛን በመውደድ ፤ ቁጭ ብለን የሕይወትን ትምህርት እንማርበት ዘንድ ጊዜ የለንም እንዳላችሁ ፤ ባጠቃላይ ልባችሁን እንዳሰነፋችሁ ሰማንና ፤ ቀድሞ ስለእናንተ ደስ የተሰኘንበትን ነገር አስበን አዘንን። ከቶ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ " ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማነው? " ያዕ 3 ፦15-18 ያለውን አላነበባችሁምን? ... በዕውኑስ ወደ መንፈሳዊ ጥበብ ፣ ወደ መንፈሳዊ ኃይል ፣ ወደ መንፈሳዊ ተዘምዶ ከመጠራታችሁ አስቀድሞ ምን እንደነበራችሁ ፣ የትስ እንደነበራችሁ ዘነጋችሁትን? ... እንግዲህ ራሳችሁን መርምሩ!

ሰው ሰውን ... እገሌ እንደ ሰሎሞን ፣ እንደ ሲራክ ያለ ጥበበኛ ነው ፤ ያሉት እንደሆነ መክሮ አስተምሮ ጠላቴን ያጠፋልኛል ፤ መንግስቴን ያጸናልኛል ብሎ እንደሚሻው ... እንዲህ ባለ ጥበባችሁ ተጠራችሁን? ... ሰው ሰውን ... ኃይሉ እንደ ጌዲዮን ፣ እንደ ሶምሶን ፣ እንደ ዮፍታሔ ያለ ነው ፤ እገሌ ኃይለኛ ነው ፤ ያሉት እንደሆነ ክንድ ይሆነኛል ፣ ጠላቴን ያደክምልኛል ብሎ እንደሚሻው ... እንዲህ ባለ ኃይለኝነታችሁስ ተጠራችሁን? ... ሰው ሰውን ... እገሌ ተዘምዶው እንደ አብርሃም ፣ እንደ ኢዮብ ካለ ነው ፤ እገሌ ዘመዳም ነው ፤ ያሉት እንደሆነ ፤ ጥግ ይሆነኛል ፣ አንድ በር ሁለት በር ይይዝልኛል ብሎ እንደሚሻው በዚህስ ተመርጣችኋልን? ... ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስስ " አስቀድመው ጠቢባን ፣ ኃያላን ፣ ዘመዳም ነን የሚሉ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ምላሽ ያሳጣቸው ዘንድ በዚህ ዓለም ሰንፈው የነበሩ ፣ ደክመው የነበሩ ፣ እና ከቁጥር ያልገቡ ዓሳ አስጋሪ ፣ ልብስ ሠፊ ሐዋርያትን መረጠ "  1ቆሮ 1 ፦ 20 አለ። ... ታዲያ እናንተስ መጠራታችሁ ከእንደዚህ ያለ ነገር አይደለምን? ... እንግዲህስ እግዚአብሔር በሚያውቀው ነገር ሥጋዊ ደማዊ ሰው ሁሉ ጥበበኛ ነኝ ፣ ኃይለኛ ነኝ ፣ ዘመዳምም ነኝ ፣ ... እያለ እንዳይመካ ... የሚመካስ በእግዚአብሔር ይመካ!

ወንድሞች ሆይ ፦ እኛስ በዚህ ማኅበር ያለን ወንድም እህቶቻችሁ በመማራችሁ የምታገኟቸው ጥቅማጥቅሞች ፤ እግረመንገዳችሁን የምትቀበሏቸው ሽልማቶች እንጅ የመመራመራችሁ የመጨረሻ ግቦች አይደሉም እንላለን። ... ይልቁንስ በቆይታችሁ ተጨባጭ ክሂልንና ተገቢ ውሳኔን ፤ ብልህነትንና አስተዋይነትን እንድትይዙ እንመክራችኋለን። ምክንያተኝነታችሁንም ትታችሁ በምድራዊ እውቀታችሁ ላይ ሰማያዊውን ጥበብ ታክሉበት ዘንድ ፤ ምድራዊውን በሰማያዊው ታስጌጡት ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንለምናችኋለን።

በቀረውስ ሥንፍና ካላችሁት ጌታችንን ፤ መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ የሚሰነፍ ሥንፍና ከሰው ጥበብ አይበልጥምን? ... እውነት እውነት እንላችኋለን ፤ ሐና ፣ ቀያፋ ቢሏችሁ ሁለት ሦስት ቋንቋ አያውቁም ነበር ፤ ክርስቶስን የሰበኩ ሐዋርያት ግን በሰባ ሁለት ቋንቋዎች ተናግረዋል። ቅዱስ ጳውሎስ " ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዚህን ዓለም ሰነፎች መረጠ ፤ አለን የሚሉትንም ያሳፍር ዘንድ ዘመድ የሌላቸውንና  ከቁጥርም ያልገቡትን መረጠ ፤ እግዚአብሔር የተከበረውን እንደሌለ ለማድረግ በዚህ ዓለም ዝቅ ያለውንና የተናቀውን ነገር ፤ ቦታ ያልተሰጠውን ነገር መረጠ " 1 ቆሮ 1 ፦ 27-29 እንዳለ።

ታዲያ እንዲህ ተሰብኮላችሁ ሳለ ይህንን የመሰለውን ስንፍና ፤ ክፉ ሐሳብ እያመላለሳችሁ በከንቱ መድከማችሁ ፤ ህሊናችሁ አስቦ ሊደርስበት ለማይችለው ፣ ታላቅና ልዩ ለሆነ ዓላማ የጠራችሁን ፤ ጌታችሁን ኢየሱስ ክርስቶስን አያሳዝንምን? ... አሁንስ ልብ አድርጉና ወደ ማስተዋላችሁ ተመለሱ ፤ ዘወትር ወደ ቤተክርስቲያን ለመገስገስ ፣ ቤተክርስቲያን የምታዘጋጀውን የቃለ እግዚአብሔር ማዕድ ለመሳተፍ ትጉ። ... ያን ጊዜ ጠንካራ እና ደካማ ጎናችሁን ትለያላችሁ ፤ የጎደላችሁን ትሞላላችሁ ፤ ያቅማችሁን ለመስራት ትጥራላችሁ ፤ ... ቀድሞ በተሰነካከላችሁበት ነገርስ የምሕረት መገኛ ፣ መዓቱ የራቀና ትዕግስቱ የቀረበ አምላክ ይተውላችኋል።

በተረፈ ወንድሞች ሆይ ደህና ሁኑ ፤ ፍፁማን ሁኑ ፤ በሰላምም ኑሩ ፤ የፍቅር ፣ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል ፤ ባለንበት ማኅበር ያሉ ወንድሞቻችሁ እና እኅቶቻችሁ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ፣ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር የመንፈስቅዱስም ኅብረት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።



በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/የሰንበት ት/ቤቶች
ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
አ/አ/ማዕከል ት/ሐ/አገ/ክፍል
መጋቢት 2002 ዓ.ም


No comments:

Post a Comment