መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Friday, July 30, 2010

" እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን ፍፁሙንም መርምሩ " ሮሜ 12 ፦ 2

" እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን ፍፁሙንም መርምሩ " ሮሜ 12 ፦ 2

በስመ ሥላሴ አሜን።

ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ።

" እያንዳንዳችን ...
  ቤታችንን ..
  ብንጠርግ ... ብናፀዳ
  አዲስ አበባችን ... ምን ያህል በፀዳ "
*  * * * * * * * * * * *
የማይመስል ነገር ... የማይሆን ግርግር
             ...  የቆሻሻ ክምር ...
'ራሱ ቆሽሾ ሌላውን ሊያቆሽሽ ባሰፈሰፈ አገር።

ይህችን ግጥም ቢጤ ፦ በአንድ ወቅት በመዲናችን በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የክፍለሃገር ከተሞች ሰሞነኛ አጀንዳ ሆኖ ለሰነበተና ለቅፅበት ታይቶ ለጠፋ የፅዳት ዘመቻ ነበር የሞነጫጨርኳት ...

በወቅቱ የዘመቻ ባህሪይ ከሆነ ትኩሳትና ስሜታዊነት የተነሳ የከተሞችን ገፅታ በመቀየር ሒደት የተለያዩ እና ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራት ሲሰሩ እንደነበረ የብዙዎቻችን ትውስታ ነው። ... የሆኖ ሆኖ ወደ ዘመቻ የተገባው የህዝቡን አመለካከት በማሳደግ በኩል በቂ ስራ ሳይሰራ በመሆኑ የተጠበቀው አዲስ አበባን ፅዱና አረንጓዴ የማድረግ ግብ ከፍፃሜ ሳይደርስ ... የአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ለዚህም በአዲስ አበባ ባምቢስ እና መገናኛ ድልድይ አካባቢየሚገኙ ቦታዎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል ... አምረውና ተውበው ለህዝብ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አውርተን ሳንጨርስ ወደቀደመ የቆሻሻ መነኻሪያነታቸው ተመልሰዋልና ... እንዲህም ማለቴ በጊዜው የነበረውን መነሳሳት ፤ የዚህንም መነሳሳት ግምባር ቀደም ተዋናይ ፦ የአርቲስት ጋሽ አበራ ሞላን ዋጋ ለማሳነስ ( ቸርችል ቪውን የመሰሉ ምሳሌ የሆኑና ይበል የሚያሰኙ ስራዎች የዚህ መነሳሳት እሳቤ ውጤቶች ናቸውና )  ሳይሆን የህዝቡ የአመለካከት ለውጥ ዘመቻውን ሊቀድመው ይገባ ነበር ለማለት ነው። ...


ዛሬም ታዲያ በቤተ-ክህነታችን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ ከእኛ ከምእመናን የሚሰሙት የመፍትሔ ሀሳቦች በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔርን መንጋ ይጠብቁ ዘንድ በተሾሙ የቤተክርስቲያን መሪዎች ስር ፤  ሰማያዊውን መንግስት ተስፋ ስለማድረግ ምክንያት ስለሚኖር ክርስቲያናዊ ኑሮ ያለን አመለካከት በፅዳት ዘመቻው ወቅት እንደነበረው ያለ ደካማ ስለመሆኑ የሚያሳብቁ ናቸው። ... እርግጥ ፦ በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ አስተዳደራዊ ችግር እንዳለ ከቤተክርስቲያኑ አመራሮች ተግባራት መረዳት ይቻላል ፤ ... ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ፤ በጎ ከሆነውም ፈቃዱ ፈቀቅ ከማለታቸው የተነሳ። ... ነገር ግን  ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሳ አንድ አብይ ጥያቄ ደግሞ አለ ... ' ምን ያህሎቻችን መልካሙን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መረዳት እንችላለን? ' የሚል ...በተለይ ደግሞ ልበ-አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ " ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ " መዝ 142 ፦10 ማለቱ  ፤ ፈቃዱን መረዳት ፦ 'ራስን የተወደደ መስዋት አድርጎ ከማቅረብ ጋር ወደ ፈጣሪ ሊፀለይበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ያመለክታልና ጥያቄው የበለጠ ከባድ ይሆናል። ... እንዲህስ ስለሆነ ፤ ከበደላችን የተነሳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የምንቸገር እኛ በቤቱ ለሆነው ችግር መፍትሔ እንዴት ሊታየን ይችላል? ... ከሁሉ በፊትስ ራሳችንን በጌታ ፈቃድ ስር ማኖር አይቀድምምን? ...

ብዙዎቻችን እንደሰውሰውኛ መልካም ብለን ያሰብናቸውን እሳቤዎች ሁሉ አምላክም የሚወዳቸውና ቅቡል አድርጎ የመቁጠር የተሳሳተ አመለካከት ይታይብናል ... ይህንን ነጥብ በምሳሌ ለማየት በቅዱስ መጽሐፍ በ 1ኛ ሳሙ 8-15 ሰፍሮ የሚገኝን ታሪክ እናንሳ ፦ በእስራኤል ላይ ፈራጅ የነበረ ሳሙኤል በሸመገለ ጊዜ ሁለቱን ልጆቹን ኢዮኤልንና አብያን በእርሱ እግር ሾማቸው  ፤ ልጆቹ ግን ረብ ( ጥቅም )  ለማግኘት ብለው ከእርሱ መንገድ ወጡ ፤ ፍርድንም አጓደሉ ...  እንዲህም በሆነ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች እየሆነ ካለው ነገር የተነሳ ተጨነቁ ፤ ... አባታቸውስ እያለ እርሱ ይገስፃቸዋል እርሱ ካረፈ በኋላ እንዴት ያደርጉናል ብለው ...ታዲያ በነገሩ ብዙ ከመከሩ በኋላ ለነርሱ መልካም የመሰላቸውን ሀሳብ ወደ ሳሙኤል አመጡ ... ንጉስ አንግስልንም አሉት ... መልካም ያሉት ሀሳባቸው መዓትን እንደሚያመጣባቸው የሚያዩበት መንፈሳዊ ዐይን አልነበራቸውምና ... እግዚአብሔር አምላክ በሳሙኤል አማካኝነትይንግስልን ስለሚሉት ንጉስ ክፋት እንኳ እየነገራቸው መልካም ስላሉት ሀሳብ ፈፅመው አንሰማም አሉ ... እኛም ዛሬ ከቅድስት ቤተክርስተቲያን ቅንዓት የተነሳ የቤተ-ክህነት አስተዳደራዊ ችግር እንዲህ  ቢደረግ ፣ እንዲያ ደግሞ ቢሆን ፣ እገሌ ቢነሳ ፣ እገሌ ደግሞ ቢሾም ፣ መንግስት ጣልቃ ቢገባ ፣ ... ይፈታል በማለት መላምቶችን ስንመታ እንሰማለን ... ታዲያ እዚህ ላይ ...'  ቤተክርስቲያናችን እንዲህ በመሰለ ፈተና ውስጥ ሆና እኛ ልጆቿ አንዳች መላ መፈለጋችንን ነውር አድርገህ ማቅረብህ ነውን? ' ... የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው .... ነገር ግን ይህን ማለቴ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ " እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን ፍፁሙንም መርምሩ " ሮሜ 12 ፦ 2 እንዳለ በነገሩ ውስጥ እጃችንን ከማስገባታችን አስቀድመን አካሔዳችን ምን መምሰል እንደሚገባው ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልገናል ለማለት ነው።

ምንም እንኳ ስለቤተ-ክህነት አስተዳደር በጥልቀት የማውቀው ነገር ባይኖረኝ ፤ ለመንፈሳዊ ዓላማ የተቋቋመና በመንፈስቅዱስ መሪነት የሚንቀሳቀስ መንፈሳዊ ተቋም እንዲህ ጊዜያዊ ችግር በሚገጥመው ጊዜ ፤ መፍትሔው ሊገኝ የሚችለው በእግዚአብሔር ፈቃድና ፣ እርሱ በሚወደው አካሔድ ፤ በመንፈሳዊ ሥልት ብቻ እንጅ በሌላ ከአለም በሆነ ዘዴ እና ምድራዊ ሀሳብ በበረታባቸው ሰዎች ጣልቃብነት እንዳልሆነ እምነቱ አለኝ። ... እንዲህስ ከሆነ ዘንዳ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ምንድን ነች? ... እንዴትስ እንወቃት? ... እርሱ የሚፈቅደው ፤ መንፈሳዊው አካሔድስ እንዴት ያለ ነው? ... ለሚሉት ጥያቄዎቻችን ሁሉ እኛ እርሱን ፈጣሪያችንን ከጉዳዮቻችን ፊት ማስቀደማችንን ፤ በጥቂቱ በመታመን ከገለጥን ወዲያ የሚመለሱልን ይሆናሉ!!! ... ያኔ የችግሩን መፍቻ ቁልፍ እናገኘዋለን!!! ... ከዚህም ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያን መምህራን ትክክለኛውን ጎዳና ፤ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበውን መንገድ በማመላከት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ሊወጡ ይገባቸዋል። ... እኛም በፅኑ መሻትና ፣ በበጎ ህሊና ወደ ፈጣሪያችን ልናመለክት ያስፈልገናል  እላለሁ ፤ ደግሞም ስለራሳችን ብቻም አይደለ ... መንጋውን ሊጠብቁ ስለተሾሙትም ሁሉ እንጅ ... እንዲህ ማድረጋችን  በራሱ ስለእግዚአብሔር ቤት እና ስለስርዓቱ ያለንን አመለካከት እና መረዳት ትክክለኛነት ያሳያልና ...

የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የምህረት ፊቱን ይመልስልን።

አሜን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።




23/11/2002
Tromso, Norway

No comments:

Post a Comment