መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Tuesday, July 20, 2010

ያልታደለችዋ ዛፍ

ያልታደለችዋ ዛፍ

ባንድ ወቅት የአንድ ዛፍ
ግንዱ ከቅርንጫፍ
ቅርንጫፍም ባቅሙ ከሌላ ቅርንጫፍ
ተጣሉ ይባላል ፈልገው ትርፋ ትርፍ።

ታዲያ በዚህ ነገር ስሩ እጅግ አዝኖ
ሊሸመግል ገባ በመካከል ሆኖ

ከዚያም ሽማግሌው ሁሉንም ቃኘና
እርቁን አስጀመረ እንደዚህ አለና
ስሙ አካላቶቼ ነገሬን አድምጡ
ሕይወታችን ሆኗል ከድጥ ወደማጡ።
ምንም እንኳ ምግቡ ብዙ ቢትረፈረፍ
ተፈጥሮ ቢያድለን ሁሉን ነገር በገፍ
ያው እንደምታውቁት እኔ አባታችሁ
በጎርፍ በፀሀዩ ደካማ ሆኛለሁ።
እንዲያም እንኳ ቢሆን እንደምንም ብዬ
ቁሩንም ጎርፉንም ንዳዱንም ችዬ
ለኑሮ የሚሆን ምግብ ፈላልጌ
እየላክሁላችሁ በግንድ አድርጌ
እየኖርን ነበር በሰላም ተዋደን
ችግሩን ስቃዩን በአንድነት ችለን።
ሰሞኑን ግን እኔን አልጥምህ ብሎኛል
ጠባችሁ ከባብዶ ገዛዝፎ ታይቶኛል።

በማለት አቅንቶ ግንዱን ተመልክቶ
የብዙ ቅርንጫፍ ክስን ሁሉ አይቶ
እንዲህ ሲል ወቀሰው በሀዘን ተጎድቶ

ታላቅ በመሆንህ ከሁሉ አስበልጨ
ሁሉንም ሰጠሁህ እኔ ተቀምጨ
ነገር ግን ይህንን ከምንም ሳትቆጥር
ትጎዳቸው ጀመር ምንም ባለማፈር
እንዲህ ብሎ እንኳን ተናግሮ ሳይጨርስ
ግንዱ ቱግ ብሎ ይከራከር ጀመር
ቅርንጫፎች እኮ እኔን የከሰሱት
እንዳይጋለጥ ነው የራሳቸው ጥፋት
ሁልጊዜ ሆን ብለው ይጨቃጨቃሉ
አንተ የላከኝን አስቀረህ ይላሉ
ደግሞ ሲላቸውም አዳላህ ይላሉ
እርስበርሳቸውም ይነቃቀፋሉ።
እያለ እያስረዳ በመሀከል ገብተው
ቅርንጫፎች ጮኹ ሀሰት ... ውሸት ብለው
አንዳቸው ላንዳቸው ክፉ ሲመልሱ
ጠባቸው ተካሮ ለፍጅት ደረሱ
ሽማግሌው ስርም እጅግ ቢቆጣቸው
የሚሰሙ አልሆኑም በሙሉ ሁላቸው።
ታዲያ ይህን ያዩ የጎረቤት ዛፎች
ያዘኑ በመምሰል ተጠጉ አንዳንዶች
ጠበኞችም ፈዘው ያዘኑላቸውን ተመለከቷቸው
ዛፎቹም በእጅጉ ስለደለሉዋቸው
ስሩንም ትተውት አስታርቁን አሏቸው።
ባዕዶቹም ይህን ከለላ በማድረግ
ስሩን ተጠጋጉት ጥቅም በመፈለግ
ስሩ ግን በፋንታው ሁኔታቸው ገብቶት
ላካላቱ ጮኸ ነገር ግን ማን ሰምቶት።
ዛፎቹም ጠቅሟቸው መለያየታቸው
የውሸት የውሸት አደራድረዋቸው
ምግባቸውን ሁሉ ወሳሰዱባቸው።
ከዚያም ጠበኞቹ አገርሽቶባቸው
ሲጣሉ ቆይተው ሞቱ አሉ ደራርቀው።



ምሽት 12፡00 - ተሳያት 7፡00
01/01/98
ዲላ

No comments:

Post a Comment