መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Thursday, February 9, 2012

ትንቢተ ዮናስ


ትንቢተ ዮናስ

ምዕራፍ
በሕዝብዋ መካከል ዓመፅ ስለ ጸና
በጣም ተቆጥቼ አዝኛለሁና
ይህን ለነነዌ ንገራት በአዋጅ
አለና ለዮናስ ለአሚታይ ልጅ
እግዚአብሔር አዘዘው እንዲሄድ በቶሎ
ዮናስ እምቢተኛው አሰበ ኮብልሎ
ከአምላክ ተደብቆ አምልጦ ሊጠፋ
ወደ ተርሴስ ሊጓዝ ሄደ ወደ ያፋ
ዋጋ ከፈለና በመርከብ ተሳፍሮ
እያጉረመረመ ባሕሩን ተሻግሮ
ዮናስ ተደብቆ ሲሄድ በግስገሳ
ከእግዚአብሔር ተልኮ ማዕበል ተነሳ
ታላቅ ሞገድ ሆኖ ባሕሩ ተቆጣ
መርከበኞች ፈሩ ትልቅ ሽብር መጣ
መርከቡ እንዲቀልለው እናድርግ እያሉ
አንስተው ብዙ እቃ ወደ ባሕር ጣሉ
ባሕሩም ባሰበት በጣም ተናወጠ
መርከቡ መሰለ የተገለበጠ
ሰው ሁሉ ተነሳ ጸሎት ለማድረስ
ይኽ ሁሉ ሲሆን ተኝቷል ዮናስ
ወደ ዮናስ ሄዶ የመርከቡ አለቃ
ቀሰቀሰውና ከእንቅልፉ ሲነቃ
እግዜር እንዲያድነን ከዚህ ክፉ ጥፋት
ተነስ ጸልይ አለው ይብቃህ ማንቀላፋት
በመርከብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ተሰባስበው
ተመካከሩና በነገሩ አስበው
አለ ኃጢአት ሰርቶ ከእኛ ጋር የመጣ
ለይተን ለማወቅ እንጣጣል ዕጣ
አለዚያ አንድንም ስለተባባሉ
ተሰባሰቡና ዕጣ ቢጣጣሉ
እውነትም እንዳሉት አጥፊው ሰው ታወቀ
በእምቢተኛው ነቢይ በዮናስ ወደቀ
ዮናስ ተረዳና እጁ እንደተያዘ
ያጠፋውን ጥፋት ገልጦ ተናዘዘ
ምነው ባትመጣ ተጣልተህ ከጌታ
እየው መርከባችን እንደሚንገላታ
ቁጣው እንዲታገስ ለማግኘት ጸጥታ
በል አንተው ፍረደን ምን ይበጃል ቢሉ
ዮናስ መለሰና እዚህ ያለ ሁሉ
ስለምን ይጠፋል በኔ የተነሳ
ወደ ባሕር ጣሉኝ አለብኝ አበሳ
ተመልከቱ እነሆ ሥራውን አወቀ
ጥፋቱን ገለጠ ይኸው መች ደበቀ
እሱው ከፈረደ መልሶ በራሱ
ምን እናድርግ ብለው ሊጥሉት ተነሱ
ከደሙ አንጻን ሲሉ ለእግዜር አመልክተው
ወደ ባሕር ጣሉት ዮናስን አውጥተው
በዮናስ ላይ ኖሮ የመጣው ይህ መዓት
ባሕሩ ጸጥ አለ ልክ በዚያው ሰዓት


ምዕራፍ
ዮናስን እንዲውጥ ሕይወቱን ሳይጎዳ
አንድ ትልቅ ዓሳ እግዜር አሰናዳ
ዮናስም ተውጦ በእግዚአብሔር ፈቃድ
ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ሲያድር ባሳ ሆድ
ተቀይመህ ኖሮ ከላይ ብትቆጣ
ይህን ያህል መዓት በራሴ ላይ መጣ
የባሕሩ ሞገድ እኔን አዋከበኝ
ውኃና ጨለማ ሲኦልም ከበበኝ
እያለ ባሳ ሆድ ዮናስ ሲቀመጥ
አምላኩን ለመነው በመለማመጥ
የታዛዥነትም ጠባይ እያሳየ
አዝኖ ተጸጽቶ ከልቡ ጸለየ
ምን ጊዜም ቢቆጣ ነውና መሓሪ
ፊቱን መለሰለት ታረቀው ፈጣሪ
ዓሳውም ዮናስን ውጦ ሳያስቀረው
ከባሕር ተፋና መሬት ወረወረው

ምዕራፍ
ይህንን የእኔን ቃል ስማና በቶሎ
ሄደህ ለነነዌ እንድትነግራት ብሎ
ደገመና እግዚአብሔር ዮናስን አዘዘ
ነነዌ ሊገባ ዮናስም ተጓዘ
ድምጡን ከፍ አድርጎ ነቢዩ ዮናስ
ከዛሬ ጀምሮ አርባ ቀን ድረስ
ነነዌ ጠፊ ነች ከሥር ተገልብጣ
አለና ለፈፈ የእግዚአብሔርን ቁጣ
ሳያንገራግሩ ሁሉም ስላመኑ
የነነዌ ሰዎች ተጨንቀው አዘኑ
ከትልቅ ጀምሮ ሕፃኑ ድረስ
ሕይወቱ የቆመች በሥጋ በነፍስ
ሰውም ሆነ እንስሳ ይቀበል ንስሓ
ፍጡር ሁሉ ይጹም ይለይ ከእህል ውኃ
ሁሉም ከልብ አዝኖ ማቅ እየለበሰ
ከክፉ ወደ ደግ እየተመለሰ
መቼም ወሰን የለው እግዚአብሔር ምሕረቱ
ይጸልይ አለና ይለምን በብርቱ
ንጉሱ አሳወጀ ከነመኳንንቱ
የነነዌ ሰዎች በውነት ከልቡና
መጸጸታቸውን እግዚአብሔር አየና
ፍጡር ቢለምነው እንባ እያፈሰሰ
ምሕረቱን አውርዶ መዓቱን መለሰ

ምዕራፍ
የተናገረው ቃል ስላልተፈጸመ
ዮናስ ተቆጥቶ እያጉረመረመ
እንደዚህ እያለ ጸለየ ወደ አምላክ
እኔን መጀመሪያ ነነዌ ለመላክ
አስበህ ብታዘኝ ይህንኑ አውቄ
ወደ ተርሴስ ልሄድ ጠፋሁ ተደብቄ
ምሕረትህ የበዛ መሐሪና ታጋሽ
በደል የምትረሳ ከቁጣ ተመላሽ
የቁጣህን ያህል ምሕረትህ የጠና
መሆንህን ጥንቱንም እኔ አውቃለሁና
እኔን ግን ግደለኝ ልሙት ልቀበር
ሐሰት ተናግሬ የማይሆን ነገር
አልፈልግምና ቆሜ ለመኖር
ከከተማ ወጥቶ በምስራቅ በኩል
ከወደ ዳር ሆኖ ነነዌን ሊያስተውል
ምን እንደሚያገኛት ለማየት ዮናስ
ሠርቶ ተቀመጠ አንድ ትንሽ ዳስ
እግዜር በጥበቡ አንድ ቅል አብቅሎ
ቅሉም አደገና ከፍ ከፍ ብሎ
የዮናስ ራስ እንዲያገኝ ጥላ
ለፀሓዩ ንዳድ ሆነለት ከለላ
በዚህ በቅል ነገር ዮናስን ደስ አለው
እንዲህ ቶሎ ደርሶ ስለገላገለው
እግዜር በማግስቱ ጧት በማለዳ
ቅል የሚበላ ትል ፈጠረ አሰናዳ
ትሉ ቅሉን በልቶ በፍጥነት ደረቀ
ፀሓይ ወጣችና ጊዜው በጣም ሞቀ
እግዜር አዘዘና ትኩስ ነፋስ መጣ
የሚከለልበት መጠጊያ ስላጣ
ቅሉ ደረቀና ንዳድ ቢያቃጥለው
ዮናስ ተበሳጭቶ ለአምላክ እንዲህ አለው
እንደዚህስ ሆኜ ቆሜ ከምኖር
እባክህ ግደለኝ ልሙት ልቀበር
ደረቀብኝ ብለህ ይህን ቅል በማጣት
እውን ይገባል ወይ የአንተ አሁን መቆጣት?
ብሎ እግዜር ቢጠይቅ መለሰ ዮናስ
በንዴት ብዛት እስክሞት ድረስ
አዎን ይገባኛል መናደድ መጤስ
እግዜርም መለሰ ለምን ጠፋ ስትል
ይህ ያልለፋህበት ያልደከምህበት ቅል
አንተ ስትናደድ ፈጥሬያት እኔማ
ሳጣፋት ሳፈርሳት ነነዌን ከተማ
መቶ ሃያ ሺ ነው የሕዝብዋም ብዛት
ለምን ትቆጣለህ እኔ ባዝንላት
ብሎ በምሳሌ ሲያስተምር ይቅርታ
ለዮናስ ነገረው የምሕረቱ ጌታ
ለእግዚአብሔር ቸርነት ምስጋና ይድረስ
በዚህ ተፈጸመ ትንቢተ ዮናስ


የዕውቀት ብልጭታ, ገፅ ፸፰
እጅጉን መወደድና መከበር የሚገባቸው ዶ/ር ከበደ ሚካኤል

No comments:

Post a Comment