መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Thursday, May 3, 2012

የበፍቃዱ ሞረዳን የ ’ትውልዴ መዝሙር’ እንካችሁ ለቅምሻ


የእኔ አባት ይሻላል

ቋጥኝ ከስካሹ
ኩይሳ ፈርካሹ
ኮርማ ጠምዶ አራሹ
ተልሞ ገስጋሹ
ገስግሶ ደራሹ
አልሞ ተኳሹ
አስቦ ወሳኙ
ወስኖም ከዋኙ
ግድ የለው ለሆዱ
ሀቅ ናት መንገዱ
 የእኔ አባት ይሻላል
ካ’ያ ባለድግሪ …
አጎንብሶ አዳሪ
የእኔ አባት ይሻላል
ያምርበታል ድግሩ
ማረሻ ወገሉ
እርፍና ሞረዱ
ካገር አደራ በል
ከምሁር ገመሬ
የእኔ አባት ይሻላል
ማይሙ ገበሬ
ዘር ያመርታል ፍሬ


ዕውነት በሰው ቁመት

አወይ ሰው ምስኪኑ
ሲጎልበት ቀኑ
በደከመ ጎኑ
ፅኑዎች የሆኑ
በ’ርሱ እንዳይጨክኑ
አቤት መማፀኑ
*************
አቤት ሰው ምስኪኑ
ሲመቸው ዘመኑ
በፀናበት ጎኑ
ደካሞች የሆኑ
እንደርሱ ካልፀኑ
ወይ አጨካከኑ


አለመታደል

የየዘመን ረመጥ
በነደደ ቁጥር
ለጣደን ስንጣድ
ጉልቻ ስንቆጥር
ጉደኛ ነፍሳችን
አትበስል አትከስል
ትገላበጣለች
ጥቢኛ ትመስል


ለዲዮጋን ልጆች/ክፍል ሁለት/

ማነው የሀቅ ወገን - ማነው የሰው ተስፋ
ሃገሬ ሃገሬ - ብሎ ቢደነፋ
ንግግሩ ቢከር - ትንታው ቢሰፋ

… ሰው የለም አትልፋ …
… ብቻ ደግነቱ …

የታጣው ሰው ሁሉ - ጠፍቶ አለመጥፋቱ
አለሁ የሚልበት - አንድ ቤት መቅረቱ
አንድ ጠባብ ክፍል - ከውስጥ ያ ከተፎ
ማንም እንዳይገባ - መዝጊያውን ቆልፎ

       በላላ ቀበቶ - በታጠፈ ጉልበት
       ሱሪውን ዝቅ አርጎ - በተቀመጠበት
       ሰው አለ! ይልሃል - ድምፁን አጎርንኖ
       የሰው ልጅ መገኛው - እዛ ብቻ ሆኖ

No comments:

Post a Comment