እውን አንተን ወለደ!?
ለተረት ተረትህ ድርጎ ፤ መሞገትን ባትወድም
እኔ ከአንተ መልስ እሻለሁ ፤ መቸም ላንተ ወሬ አይገድም
አስጠብቦ አያስጨንቅም
ከጀርባ ላብ አያፈልቅም።
መልስ ቢጠየፍ ህሊናህ ፤ ፌዘኝነትን ወዶ
ከአባትህ የስልጣኔ ሀሁ ፤ አቡጊዳህ ተወላግዶ
ከልጅህ ማነን? ጥያቄ ምላሽህ ተካክዶ
ቢሆንም ያለኽው ቅሉ ፤ ያባትክን አጽም አስታመህ
ባባትህ ብርሃን ጨልመህ
በስልጣኔው ሰይጥነህ
ቢሆንም ያለኸው ቅሉ
አበው መጠየቅ አይከብድም አሉ
እስቲ ልጠይቅህ ያንተ ማነው አባትህ?
ያ ስልጣኔንን ቀድሞ የማለደ
በማይነቅዝ ግዙፍ ግብሩ ፤ አዲስ ብርሃን የቀደደ
ያ ባየር በረህ ፤ የምታየውን ታምር
ባልተጸነሰ ቴክኖሎጅ ፤ የማይጠፋ ቅርስ ያኖረ
ያ የላሊበላን መቅደስ ፈልፋይ የአክሱምን ሀውልት ጠራቢ
የጣናን ደብሮች ደባሪ የፋሲልን ግንብ ገንቢ
ያ ስልጣኔን ቀድሞ የማለደ
እውን አንተን ወለደ!?
አባትህ፦
የዘመን እጣ ድርሻውን ፤ ከህይወቱ ተጣጥሎ
ከእውቀት አድማሱ ባሻገር ፤ ለግብሩ ካስማ ቸክሎ
ባድማሱ ውስጥ አሸልቦ ፤ ካድማስ ማዶ እያለመ
በህሊናው ቋት መዝኖ አድቅቆ እያለመ
አዲስነት እንዳጓጓው
ስልጣኔ እንዳተባው
የዘመንን ፈተና ጥሎ ፤ ጭላንጭል እንዳጮለቀ
እንደ ዳመና ግላጭ ስጥ ፤ እርካታ እንደናፈቀ
በነገ ብርሃን ድምቀት ፤ በተስፋ እንደታረቀ
አንተን ልጁን አፈራ ፤ ለእርሱም ለሀገሩም ግራ።
አባትህ፦
እኔ ከሞትኩን ሳይተርት ፤ ከቡሊት ጋር አብሮ
የማይሞከረውን ሞክሮ
የማይደፈረውን ደፍሮ
ሁዋላ ቀር ብትለውም ፤ ህሊናውን አስጠብቦ
ተአምር ብትለውም ፤ ያቆየውን ዘግቦ
ለራሱ ሳይሆን ለሀገር አስቦ
እንዳንተ ጥያቄ ሳይፈራ ፤ እራሱን እየጠየቀ
ልራቀቅ ብለህ ብትርቀውም
አሮጌ ብለህ ብትንቀውም
በብራና እየከተበ
ታሪክ እየዘገበ
አለት እየፈረፈረ ድንጋይ እየጠረበ
ያቆየውን ታሪክ ታምር ባይ ፤ እውን አንተን ፈጠረ!?
ያ አባትህ ስልጣኔን ቀድሞ የማለደ
ማን ይሙት አንተን ወለደ!?
«አባቴ ይሙት» እንዳትለኝ ፤ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ
ትጉህ ወራሽ በማጣቱ
ቦዩ በመገደቡ ጉዞው በመገታቱ
የእሱ እረፍት ሞት አይደለም ፤ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ።
መቼም መጠየቅ ሞትህ ነው ፤ ድካሙን አትመርምረው
የላሊበላን ድንጋይ እንዴት እንደቦረቦረው
የአክሱምን ግግር አለት እንዴት እንደጠረበው
የዝዋይን የጣናን ደብር እንዴት እንደደበረው
ድካሙን አትመርምረው።
ደገፍ ብለህ ፎቶ ተነስ ፤ ግርግዳህ ላይ ስቀለው
አየሁት ብለህ ታወራለህ ፤ በቪዲዮ ቅረፀው
ላንተ የሚበጅህ ያ ነው።
እንዴት ሰራው ካልክማ ፤ በጥያቄ ከተጠበብክ
አሰራሩን ካሰላሰልክ ፤ በህሊናህ ተወለጀልክ።
እኔስ ምን ሰራሁ ካልክማ
ከህሊናህም አትስማማ።
ታምር ነው! ካልክ ይበቃል
ማን ባርምሞ ይታዘብሃል ፤ አባትህ እንደሁ ሞቷል።
አድጎ ባምሳልህ እስክትቃኘው ፤ ልጅህ እንኳን ቢጠይቅህ
ላሊበላ በምን ተሰራ? አክሱም እንዴት ቆመ? ቢልህ
በቅሎ ነው ብለህ ንገረው ፤ መሬት ፈንቅሎ ወጥቶ
ታምር ነው ይበል እሱም ፤ በታምራትህ ተቃኝቶ።
አባትህ፦
ታምር ነው ስትል በሰማህ ፤ ያላሰበውን ሰጥተህ
በስንፍናህ አገዛዝፈህ
ከመላእክት ተርታ ስታስገባው ፤ ምድራዊ ጥረቱን ክደህ
እንዲህ ሳትሞት ሞተህ
ቢያይህ …
ለሱ ታምር ያ ነው ፤ ያልዘራህ አንተ መብቀልህ
ለሱ ያ ነው መርገምቱ
ቢሞትም ዳግማዊ ሞቱ።
አባትህ፦
ምላሱን በጥርሱ ነክሶ ፤ በግብሩ በተናገረ
የሀገሩን የኪዳን ቃል ፤ ባህር ተሻግሮ ባስተማረ
የዜግነት ውግዘት ሳይነካው ፤ ሀገር ምስጢርዋ ገኖበት
ሰንደቅ ግርማዋ ደምቆበት
የኖረበትን ዘመን ፤ በግብሩ ስንዝር እየለካ
ኋላቀር የምትለውን ፤ እውን አንተን ይተካ!?
«አባቴ ይሙት» እንዳትለኝ ፤ አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ
ትጉህ ወራሽ በማጣቱ
ቦዩ በመገደቡ ጉዞው በመገታቱ።
ጉድና ጅራት ኋላ ነው ፤ አንተም ያባትህ ጉድ ነህና
ተረት ተረት ቁጭ በልና …
«ሮሀ በሚባል መንደር ፤ በተራራ በታጠረ
አንድ ንጉስ ነበረ …
ከእናቱ ማህጸን ሲወጣ ፤ ገና ከመወለዱ
በንቦች የተተለመ ፤ የወደፊት መንገዱ
የአምላክ የእውነት ቃሉ ፤ ትንቢት አይቀርምና
አድጎ ዙፋኑን ጫነ ፤ በረከቱን ተቀባና
ከዚያማ ምኑ ቅጡ! እግዜር እጁን ጫነበት
ብርሃኑን አካፈለው ፤ መንፈስቅዱስ እፍፍፍ አለበት
በብርሃን አምድ አመልክቶ ፤ ብርታቱን ሰጠውና
ቤተመቅደስ እንዲያንጽ ፤ ሃይማኖቱን እንዲያቀና
ለይስሙላ እጁን ሲያነሳ ፤ መላእክት ተረባርበው
የማይቻለውን ችለው
ይኸውልህ ይህን ሰሩ ፤ በሱ አካል እነሱ አድረው»
እያልክ ለልጅህ ተርተው
ያምላክ ትንግርት አድርገህ
ያባትክን ድካም ክደህ።
ያኔ ህሊናህ ይጃጃላል ቆስሎ … መግሎ … አይጠነባ
በባዶ ሞራህ ተሸብልሎ ፤ ከከርስህ ውስጥ ነው ‘ሚገባ
አባትህ፦
ጊዜውን በሰዓት ሳይሆን ፤ በስራው ፍሬ እየለካ
ድካሙን ትንግርት ባይ ፤ እውን አንተን ይተካ!?
ያ የላሊበላን መቅደስ ፈልፋይ የአክሱምን ሀውልት ጠራቢ
የጣናን ደብሮች ደባሪ የሐረርን ግንብ ገንቢ
ያ ስልጣኔን ቀድሞ የማለደ
የዘላለም ቅርሱን ተራች ፤ እውን አንተን ወለደ!?
እውን አንተን ወለደ!?
ትንግርት ነን።
በድሉ ዋቅጅራ (ፍካት ናፋቂዎች, 1999 ዓ.ም.)
No comments:
Post a Comment