በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ትምህርተ ሃይማኖት በጸሎተ ሃይማኖት
ውድ አንባቢያን ወገኖቼ ሆይ ፤ የሰው ልጅ በዓመፅ ፣ በእምቢተኝነት ፣ በቸልተኝነት ፣ በዝንጋኤ ፣ በግዴለሽነት ወይም በልዩ ልዩ ዓለማዊና ምድራዊ አኗኗር በተለይም አእምሮን በሚያሳጣ በክፉ ልማድ ተጠምዶ ፤ በልቡናው ያለውን የእግዚአብሔር ዕውቀት ወይም እምነት ካልተወ በቀር የሃይማኖት ስሜትና አሳብ ፈፅሞ አያጣም። ከዚህም ስሜቱና አሳቡ የተነሳ በፍኖተ አእምሮ ፣ በእግረ ልቡና በመመራት ይልቁንም በመጀመሪያ በቤተ እስራኤል ቀጥሎም በቤተ ክርስቲያን በሆነው የእግዚአብሔር መገለጥ ፈጣሪውን ወደማመን ይደርሳል። ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንም ይህን አስቀድሞ በትንቢት ፣ በታሪክና በምሳሌ ኋላም በአማናዊነትና በፍጹምነት የሆነውን መገለጥ ለሁሉም ወገኖች ታስተምራለች ፤ አስተምህሮዋም በጸሎተ ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ፤ ቢያውቁት ፣ ቢረዱትና ጸንተው ቢኖሩበት የኅሊና ሰላምን የሚሰጥና ደኅንነትን የሚያስገኝ ነው።
ጸሎተ ሃይማኖት ታሪካዊ አነሣሡ ምንም እንኳ መናፍቃንን ለመለየትና ምእመናንንም በትክክለኛው ሃይማኖት እንዲጸኑ ለማድረግ ታስቦ በጉባኤ ኒቂያ (325 ዓ.ም.) እና በጉባኤ ቁስጥንጥንያ (381 ዓ.ም.) የተወሰነ ቀኖና (ሕገ) ሃይማኖት ቢሆንም ፤ የትምህርቱ ይዘት ግን ከጥንት ጀምሮ በጌታና በሐዋርያት ትምህርት ውስጥ የነበረ ነው። የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደ ዛሬው ሳይከፋፈሉና ሳይወጋገዙ ፤ በኅብረትና በአንድነት በሚሰሩበት ጊዜ የነበሩ መንፈሳውያን የሃይማኖት መሪዎችና ሊቃውንት አባቶች ይህን ጸሎተ ሃይማኖት ከቅዱሳን መጻሕፍት አውጣጥተውና በ12 ክፍሎች ከፍለው በማዘጋጀት የክርስትና መሠረተ እምነት ሆኖ እንዲሠራበት በውሳኔአቸው ለአብያተ ክርስቲያናትና ለምእመናን ሁሉ አስታውቀዋል አውጀዋል።
ከዚህ ቀጥሎ አሥራ ሁለቱን የጸሎተ ሃይማኖት አንቀጾች በመከተል ለየኃይለ ቃላቱ ከቅዱስ መጽሐፍ የሚመስላቸውንና የሚስማማቸውን ጥቅስ ለአብነት በማምጣት ለማሣየት ተሞክሯል።
መልካም ንባብ …
1. ነአምን በአሐዱ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኩሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ/ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን
1.1. ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ … (ሥነ ፍጥረት)
v «በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ምድርም ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም … » ዘፍ 1፥ 1-28
v «አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ ምድርንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ፈጥረሃል …» ነህ 9፥ 1-6
v «ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም» ዮሐ 1፥ 3
1.2. በአንድ አምላክ …
v «ያለና የሚኖር እኔ ነኝ» ዘጸ 3፥ 14
v «እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው» ዘዳ 6፥ 4
v «ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሰራ በሁሉም የሚኖር የሁሉ አባት እግዚአብሔር አንድ ነው…» ኤፌ 4፥ 6
1.3. በእግዚአብሔር አብ … (ምሥጢረ ሥላሴ)
v «እኔ ከእግዚአብሔር አብ ወጥቼ መጥቻለሁና» ዮሐ 8፥ 42
v «እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል» ዮሐ 15፥ 26
v «የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ …» 1ዮሐ 3፥ 1
ማስታወሻ፦ እግዚአብሔር አብ (አባት) ብቻውን አብ (አባት) እንደማይባልና ከእርሱ ጋር የባሕርይ ልጁ ወልድ ዋሕድ እንዳለ መረዳት ፤ በተጨማሪም ከእርሳቸው ጋር ደግሞ የባሕርይ ሕይወታቸው እስትንፋሳቸው መንፈስቅዱስ እንዳለ ማስተዋል ይገባል።
1.4. እናምናለን …
v «እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው» ዕብ 11፥ 1
v «ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም … ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ (እንደነበረ እንደሚኖር) ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል» ዕብ 11፥ 6
v «እምነት መሠረት ነች ሌሎቹ ግርግዳና ጣራ ናቸው» ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
2. ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም/ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን
2.1. ዓለም/ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ …
v «በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» ዮሐ 1፥ 1 2
2.2. የአብ አንድ ልጁ በሚሆን …
v «አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ» መዝ 2፥ 7
v «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው» ማቴ 3፥ 17
v «አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ» ማቴ 16፥ 16
2.3. በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን …
v «ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል» ሉቃ 2፥ 11
v «መዳንም በሌላ በማንም የለም ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለም» ሥራ 4፥ 12
v «እውነተኛ በሆነው በእርሱ አለን እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው» 1ዮሐ 5፥ 20
3. ብርሃን ዘእምብርሃን አምላክ ዘእምአምላክ ዘተወልደ ወአኮ ዘተገብረ ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ/ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል
3.1. ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ …
v «ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድኩህ» መዝ 109፥ 3
v «በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ … ያም ቃል ሥጋ ሆነ» ዮሐ 1፥ 1 14
v «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው ሁሉንም በፈጠረበት በልጁ ነገረን እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የመልኩ ምሳሌ ሆኖ …» ዕብ 1፥ 1 4
3.2. የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ …
v «እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች» ኢሳ 7፥ 14
v «ሕጻን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል» ኢሳ 9፥ 6
v «እነሆ ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱም ታላቅ ነው የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል» ሉቃ 1፥ 31
3.3. በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል …
v «እኔና አብ አንድ ነን» ዮሐ 10፥ 30
4. ዘቦቱ ኩሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ ዘበሰማይኒ ወአበምድርኒ/ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የለም በሰማይም ያለ በምድርም ያለ
v «አቤቱ አንተ አስቀድሞ ምድርን መሠረትህ ሰማያትም የእጆችህ ሥራዎች ናቸው» መዝ 101፥ 25
v «ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም» ዮሐ 1፥ 3
v «እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና» ቆላስ 1፥ 15
5. ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኃኒትነ ወረደ እምሰማያት ተሰብአ ወተሰገወ እመንፈስቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል/ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለ መዳናችን ከሰማይ ወረደ በመንፈስቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈፅሞ ሰው ሆነ
5.1. ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለ መዳናችን ከሰማይ ወረደ …
v «ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም … በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጅ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶታልና» ዮሐ 3፥ 14- 17
v «እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ባለጸግነትና በወደደን በፍቅሩ ብዛት በኃጢአታችን የሞትን ሳለን በክርስቶስ ሕይወትን ሰጠን» ኤፌ 2፥ 4
v «እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት አድርጎ እንደላከው እንመሰክራለን» 1ዮሐ 4፥ 14
5.2. በመንፈስቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈፅሞ ሰው ሆነ … (ምሥጢረ ሥጋዌ)
v «በመንፈስቅዱስ ጸንሳ ተገኘች … » ማቴ 1፥ 18
v «የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ» ገላ 4፥ 4
v «መሥዋዕትንና መብዐን አልወደድህም ሥጋን አዘጋጀህልኝ እንጅ» ዕብ 10፥ 5
6. ኮነ ብእሴ ወተሰቅለ በእንቲአነ በመዋዕለ ጲላጦስ ጴንጤናዊ ሐመ ወሞተ ወተቀብረ ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት በከመ ጽሑፍ ውስተ ቅዱሳት መጻሕፍት/ሰው ሆኖ በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ ታመመ ሞተ ተቀበረም በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ
6.1. ሰው ሆኖ በጴንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ ታመመ ሞተ ተቀበረም … (ነገረ መስቀል)
v «እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን … ተጨነቀ ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም …» ኢሳ 53፥ 1- 12
v «ጌታችን ኢየሱስም ሆምጣጤውን ቀምሶ ሁሉ ተፈጸመ አለ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ» ዮሐ 19፥ 30
v «በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ ነው እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ» 1ጢሞ 2፥ 3- 6
6.2. በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ … (የክርስቶስ ትንሣኤ)
v «እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ» መዝ 77፥ 65
v «አትደንግጡ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትሻላችሁን? ተነስቷል በዚህስ የለም» ማር 16፥ 6
v «ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ? የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሳትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን» 1ቆሮ 15፥ 55
6.3. በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ …
v «እናንተ የማታስተውሉ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት የተጻፈውን ተረጎመላቸው» ሉቃ 24፥ 25
v «ከሙታን ይነሳ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበር …» ዮሐ 20፥ 9
7. ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኮንን ሕያዋነ ወሙታነ ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግስቱ/በክብር ወደሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም
7.1. በክብር ወደሰማይ ዐረገ …
v «እግዚአብሔር በእልልታ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ» መዝ 46፥ 5
v «እስከ ቢታንያም ወደ ውጭ አወጣቸው እጁንም አንስቶ በላያቸውም ጭኖ ባረካቸው እየባረካቸውም ራቃቸው ወደ ሰማይም ዐረገ» ሉቃ 24፥ 50
v «ይህንም እየነገራቸው ከፍ ከፍ አለ ደመናም ተቀበለችው እነርሱም ወደ እርሱ እያዩ ወደ ሰማይ ዐረገ» ሥራ 1፥ 9
7.2. በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ …
v «ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው» መዝ 110፥ 1
v «በእስጢፋኖስም ላይ መንፈስቅዱስ መላ ወደ ሰማይም ተመለከተ የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ» ሥራ 7፥ 55
v «በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀምጦ ያለ መላእክትና ሥልጣናት ኀይላትም የተገዙለት ነው» 1ጴጥ 3፥ 22
7.3. ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም …
v «እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል» መዝ 49፥ 2
v «እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል የምድር ወገኖችም ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ» ራዕ 1፥ 7
v «እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ» ራዕ 22፥ 12
8. ወነአምን በመንፈስቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረፀ እም አብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት/ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሠረፀ በመንፈስቅዱስም እናምናለን እንሰግድለትና እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት የተናገረ
8.1. ጌታ ማኅየዊ በሚሆን …
v «የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ» ኢዮ 33፥ 4
v «በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ ሠራዊታቸውም በአፉ እስትንፋስ» መዝ 32፥ 6
v «እርሱ ራሱ መንፈስቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል እርሱም ልባችንን ይመረምራል ልብ የሚያስበውንም እርሱ ያውቃል ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ ይፈርዳል» ሮሜ 8፥ 26
8.2. ከአብ በሠረፀ በመንፈስቅዱስም እናምናለን …
v «እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል» ዮሐ 15፥ 26
8.3. እንሰግድለትና እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት የተናገረ …
v «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር …» ኢሳ 6፥ 3
9. ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት/ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቡዋት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን
9.1. ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቡዋት …
v «በዚህችም ዕለት ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ተጨመሩ በሐዋርያት ትምህርትና በአንድነት ማዕድን በመባረክ በጸሎትም ጸንተው ይኖሩ ነበር» ሥራ 2፥ 41
v «እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያን የሾማቸው አስቀድሞ ሐዋርያትን ሁለተኛም ነቢያትን ሦስተኛም መምህራንን … ነው» 1ቆሮ 12፥ 27
v «በሐዋርያትና በነቢያት መሰረት ላይ ታንጻችኋል …» ኤፌ 2፥ 19
9.2. በአንዲት …
v «ኅብስቱ አንድ እንደሆነ እንዲሁ እኛም ብዙዎች ስንሆን አንድ አካል ነን ሁላችንም ከአንድ ኅብስት እንቀበላለንና» 1ቆሮ 10፥ 17
v «እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል» 1ቆሮ 12፥ 13
v «ጌታ አንድ ነው ሃይማኖትም አንዲት ናት ጥምቀትም አንዲት ናት» ኤፌ 4፥ 5
9.3. በቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን …
v «የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጅ በላይዋ እድፈት ወይም ርኩሰት እንዳያገኝባት ቤተክርስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ» … ኤፌ 5፥ 25
10. ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት/ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን
v «ያመነ የተጠመቀ ይድናል» ማር 16፥ 16
v «በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደ ተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን» ሮሜ 6፥ 4
v «ጌታ አንድ ነው ሃይማኖትም አንዲት ናት ጥምቀትም አንዲት ናት» ኤፌ 4፥ 5
11. ወንሴፎ ትንሣኤ ሙታን/የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን (ምሣጢረ ትንሣኤ ሙታን)
v «ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ ሬሳዎችም ይነሳሉ» ኢሳ 26፥ 19
v «በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ» ዮሐ 5፥ 29
v «አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል … ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና» 1ቆሮ 15፥ 12
12. ወሕይወተ ዘይመጽእ ለዓለመ ዓለም አሜን/የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን
v «እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን ወራሾቹ ነን የእግዚአብሔር ወራሾቹ ከሆንም የክርስቶስ ወራሾቹ ነን በመከራ ከመሰልነውም በክብር እንመስለዋለን» ሮሜ 8፥ 17
v «ዐይን ያላየው ጆሮም ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ነው» 1ቆሮ 2፥ 9
v «ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» ራዕ 21፥ 1
My beloved, recite the Orthodox Creed with the whole church carefully. Believe every word as it is the fruit of the work of great Ecumenical Councils instituted by great church fathers who were guided by the Holy Spirit (ወዳጆቼ ሆይ ፤ የኦርቶዶክስ ጸሎተ ሃይማኖትን ከመላው ቤተክርስቲያን ማለት ከጉባኤው ጋር ሆናችሁ በጥንቃቄ በሉት (ድገሙት) ፤ በመንፈስቅዱስ በተመሩ በታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶች የተመሠረቱት የታላላቆቹ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤዎች የሥራ ፍሬ እንደ መሆኑ መጠን እያንዳንዱን ቃል እመኑ) Bishop Mettaus, How to Benefit from the Holly Liturgy Part One (The Bishopric of Youth Library, Dar El Geal Press, January 2000) pp 94-95
ማስታወሻ፦ ጠለቅ ላላ ጥናት የሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለን ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት የተሰኘ መጽሐፍ ከገፅ 59-221 ማየት ተገቢ እንደሆነ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ።
ምንጭ፦
መጽሐፍ ቅዱስ
ብርሃኑ ጎበና, ዓምደ ሃይማኖት አዲስ አበባ(1985) ዓ.ም.
አባ አበራ በቀለ,(ሊቀ ጉባኤ),ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት አዲስ አበባ(1996) ዓ.ም.
ስብሐት ለእግዚአብሔር።
No comments:
Post a Comment