ከንፈሩ ሳይሆን ... ሀሳቡ ሲሰነጠቅ
“ ... ተውስጥ ሲያስተጋባ የወንጀሉ ትዕዛዝ ሥርዓትና ሕጉ
አሜን ብቻ ሆነ የመሃይምን ወጉ! “
ጸጋዬ ወይን ገብረ መድኅን (ናስተማስለኪ)
በዕውቀቱ ስዩም
እግር አልባው ባለክንፍ
አንድ ባልንጀራዬ በኢ-ሜይል በጻፈልኝ መልዕክት ላይ ሰሞኑን በእምነታችን ዙሪያ ማጉረምረሜ እንዳልተዋጠለት ጠቅሶ “ እሱን ትተህ ባስተዳደሩ ላይ ብታተኩር ወንድ ትባል ነበር “ በማለት ምክሩን ለገሰኝ። አልተገናኘንም ወንድሜ እኔ አምዱን ያስከፈትሁት ባሕታዊውን ታሪካችንን በዓለማዊ መነፀር ለማዬትና ለመተርጎም አስቤ ነው ። እምነትና አስተዳደር ተነጣጥለው በሚቆሙበት ማሕበረሰብ ውስጥ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ነጥሎ መተንተን ይቻል ይሆናል ፤ የእኔና የአንተ ማሕበረሰብ ግን የቄሳርና የእግዚአብሔር ጥምር መንግስት ውጤት ነው። አንዱን ካንዱ ነጥሎ መመልከት ብዙ አይሳካም።
በዚያው እንቀጥል፦
የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክና ባህል ባንዱ ገፅ ስናየው ሃይማኖታዊ ነው። ግን ሃይማኖታዊ ባህል ይዘው በምድር የተሳካላቸው ማህበረሰቦች አይጠፉም ፤ የኛ ሃይማኖታዊነት የባሰ ነው ፤ ምናልባት ተክለሃይማኖታዊ ነው የሚለው የተሻለ ይገልጸዋል። በገድላቸው እንደሰማነው ፤ አቡነ ተክለሃይማኖት ብዙ አመታት ቆመው በመጸለያቸው እግራቸው ተሰበረ። ፈጣሪም በገድላቸው ጽናት ተደስቶ ደርዘን ሙሉ ክንፍ ሸለማቸው። ታሪኩ ተፈፅሟል ወይስ የደብተራ ፈጠራ ነው የሚለው እዚህ ገፅ ላይ አያሳስበንም ፤ ግን በግሌ ሚዛን ስገመግመው ለጻድቁ የቀረበላቸው ካሳ የሚበጃቸው አልመሰለኝም ፤ በምድር ተወስኖ ለሚኖር ሰው ለእግር እጦት ክንፍ ጥሩ ማካካሻ አይደለም። እግሩን ላጣ ሰው ፈጣንና ብርቱ እግር ቢተካለት በጣም ይጠቅመዋል ፤ አባታችን ፀሎታቸውና ድካማቸው ከምድር ጋር የሚያቆራኛቸውን ሕዋስ አሳጣቸው ፤ የሰማዩን አስተዋጽዖዋቸውን የሰማዩ ጌታ ይገምግመው ፤ በምድር ኃያላን መካከል ግን በሚደረግ ሩጫ ግን እንደማይሳካላቸው እርግጠኛ ነኝ። የጥንቱ ባለቅኔ ይሄ የገባው ይመስለኛል ፤ ጻድቁን በማስመልከት እንዲህ ብሎ ተቀኝቷል።
... ለገቢረ ፤ጸሎት አዝለፈ
ብሂሉ አውርድ ዘተሰቅለ ክንፈ
ዘአኀዞ ሰኮና ገደፈ
(ትርጉም)
ጸሎትን ያዘወተረ (አብዝቶ የተማለለ)
የተሰቀለ ክንፍ አወርዳለሁ ብሎ
የያዘውን ተረከዝ ጣለ
ባለቅኔው ጻድቁ የተሰቀለ ክንፍ ማውረዳቸውን እንኳን እርግጠኛ አይደለም ፤ “ የተሰቀለ ክንፍ አወርዳለሁ ብሎ “ የሚለው መስመር ጥርጣሬውን ይገልጣል። ተረከዛቸውን ለመጣላቸው ግን እርግጠኛ ነው።
ከሁሉ አስቀድሞ ጸሐፊው በርዕሱ ‘እግር አልባው ባለክንፍ’ ከማለቱ ተንደርድሬ አዝማሪዋ እንዳለችው ‘አያገባው ገብቶ ... ‘ ልል ቃጣኝና ... እንደ እርጎ ዝንብ እዚያም እዚህም በመርገጥ ሀሴት የሚያደርግ ሁላ፤ ‘ሀሳብን በነጻነት የመግለጥ መብት ... እኔን እስካልደረሰብኝ ድረስ’ ምናምን እያለ የሚጮኸው ጩኸት እንዳያደነቁረኝ ሰግቼ ... እኔም እንዲህ የጎረቤትን አጥር መታከክ (መነቅነቅ አልለውም -ይህ ምኑን ይነቀንቅና ... ያው መታከክ ነው) መብቱ ነው ብያለሁ ... ግና ደግሞ ተደራሲውን የማያይ ደራሲ እንዴት ያለ ነገር ነው? ... እንዴት ነው ነገሩ ይኼ ድርሰት የሚሉት ነገር ከተደራሲው በደራሲው ለተደራሲው ዓይነት ነገር አልነበረም እንዴ? ... ስል ጊዜና አንድ ፊት ገፅ ላይ አልፎ አልፎ የማያት እህቴ ወዲህ ነው ነገሩ አለችና “ Some of his writings share the same style with that of Sibhat GebreEgeziAbeHer’s who is famous for disparaging God and everything related to God. Their writings are not heretical or based on any religious stance; it is a way to become obtrusively exceptional.” ተማለቷ የእርሷኑ መነጠር ተጋርቼ ... ሚስቱን ‘አንቺን ይግረምሽ ይድነቅሽ እንጅ’ እንዳለው ባል .... ጸሐፊው የገረመውን ያህል እኔ በጻፈው ሳልገረም ቀረሁ ...
ቢሆንም አሉ አምሳ አለቃ ገብሩ ... ቢሆንም ... ጸሐፊው ተማያገባቸው እኔ ራሴ ገለል ላድርጋቸውና ... ምክንያቱሳ በቃ ስለማያገባቸው አይገባቸውማ ... ሌላ ሌላውን ትታችሁት ለተክልዬ ፈጣሪ የሸለማቸው ክንፍ ፈጣን እግር ቢሆን ጥሩ ነበር ማለት ... አንድ የጎልፍ ተጫዋች የእግር ኳስ ተጫዋቾች ስለሚያገኙት ሽልማት ፊፋን ሲከስ ዓይነት ነገር ማለት ነው! ... ታዲያ ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ፤ የሚሻለው አርፎ ጎልፉን እንዲጎልፍ መንገር ነበረ ... ግና የመክሰስና የመካሰስ መብቱን መጋፋት ስለሚሆን ትቼዋለሁ ....
እንግዲህ በሰማዩ ላይ አለቅጥ ሲያተኩር ምድሩን የሚከዳ ምድርም የምትከዳው ማህበረሰብ ተክለሃይማኖታዊ ይባላል።
አቤት ፍጥነትሽ አሉ ወይዘሮ አስካለች ... ከምክንያታዊና የተንሰላሰለ መንደርደሪያ በኋላ የቀረበ ጥግ መሆኑ ነው ... ድንቄም ምክንያታዊ ... እስቲ ይሁን
ሕሩይ ወልደስላሴ የተባሉ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ባለስልጣን በ1910 ዓ.ም. “ የልጅ ምክር ለአባት መታሰቢያ “ የሚል መጽሐፍ ጽፈው አሳትመዋል። መጽሐፉን የጻፉት በቀጥታ ለልጃቸው ፈቃደ ስላሤ ፤ በእጅ አዙር ደግሞ ልጃቸው አባል ለሆነበት ትውልድ ምክር እንዲሆን ነው። መጽሐፉ በጊዜው በተደጋጋሚ ታትሞ ተነቧል ፤ በመጽሐፉ ከተመዘገቡት ምክሮች አንዱ ‘ ልጄ ሆይ አሳብህ ሁሉ ከሞት በኋላ ወዲያኛው ዓለም ስለሚሆነው ስለነፍስህ ነገር ይሁን እንጅ በዚህ ዓለም በስጋህ ስለሚሆነው ነገር እጅግ አትጨነቅ ‘ ይላል። ምክሩ የወጣው ከባህታዊ አንደበት ቢሆን አይገርምም ፤ መካሪው ግን የአገር አስተዳዳሪ ባለስልጣን ነው ፤ የምክሩ አላማ ትውልዱ አገሩን ጥሎ እንዲመንን ለማድረግ ይሆን? ‘ በዚህ አለም በስጋህ ስለሚሆነው አትጨነቅ ‘ ማለት ‘ ልጄ ሆይ ጀዝባ ሁን ፣ ቦዘኔ ሁን ፣ ደደብ ሁን ‘ ብሎ ከመምከር ጋር በይዘት አንድ ነው። ልዩነቱ የመጀመሪያው መንፈሳዊ አቀራረብ መያዙ ነው። ደግነቱ ልጅዬው ፈቃደ ሥላሴ የአባቱን ምክር አልተቀበለም። ለሥጋው ተጨንቆ ተምሮ አገሩ በፋሺስት ጣሊያን ስትወረር ከውጭ ተመልሶ ለአገሩ ደረሰላት ፣ ተዋጋላት ፣ ሞተላት ፤ ታሪክ ሰሪዎች ሰዎች እንጅ መላዕክት እንዳልሆኑ አሳያት።
እዚህ ላይ ጸሐፊው ባለማወቅ አልያም ባጉል ድፍረት በፈቃደኝነት ለመሳሳት ቆንፅሎ ባቀረበውና እንዲሳቅለት ለሚሳለቅበት ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ጠበቃ መቆሙን እኔም በፈቃደኝነት ቸል ልበለውና (ሊገባው ስለማይፈልግ ስለማይገባው ማለቴ ነው ... ይህም መብቱ ስለሆነ!) ... ስላቁ ስለጸሐፊው ያሳበቀውን ሐቅ ብቻ ላንሳ ... የተነሳበትን እና ሊያጎለብተው ያሰበውን መልዕክት አሳማኝና ምክንያታዊ በሆኑ ጉዳዮች ከማዋቀር ይልቅ በተራ አሉባልታና ክስ አጅሎና ሸፋፍኖ የሚያልፍ መሆኑን ... እንጅማ የአገር አስተዳዳሪ ባለስልጣን ነው ብሎ ያቀረበውን ሰው ልጁን ‘ ልጄ ሆይ ጀዝባ ሁን ፣ ቦዘኔ ሁን ፣ ደደብ ሁን ‘ ዓይነት ምክር መከረ ብሎ የተነሳበትን ነገር ተራ ባላደረገ ... መቸም የአገር አስተዳዳሪ ባለስልጣንነትን እንደ ቦዘኔነት ካልቆጠረው በስተቀረ እራሱ ካነሳው መከራከሪያ ጋራ እንኳን አይሄድም ... ባጠቃላይ አባትዬው ለልጁ ያስተላለፈው መልዕክትና ጸሐፊው አንባቢዎቹ እንዲመለከቱለት ግድ የሚለው ሀሳብ እንደ ሀገሬ ሰው አባባል አልተገናኝቶም ነው።
የሕሩይ ምክር ይቀጥላል፦
“ ... ልጄ ሆይ ወደፊት እንደዚህ ያለ መከራ ያገኘኛል ብለህ አትጨነቅ ፤ ነገር ግን የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና ያለ እርሱ ፈቃድ የሚሆነው አያገኝህም። የውስጥህን የሚያውቅ እግዚአብሔር ካልፈረደብህ ንብረትህ እየሰፋ ጠላትህ እየጠፋ ይሄዳል እንጅ ምንም ክፉ ነገር አይመጣብህምና አትጨነቅ። በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚመጣውን መከራ በጉልበቴ ፣ ወይም በእውቀቴ አስቀረዋለሁ ብሎ መጣጣር በመከራ ላይ መከራ ለመጨመር ነው እንጅ ሌላ ትርፍ አይገኝበትም።
አስቡት የሰውን ጥረት በሙሉ ዋጋ የሚያሳጣ ምክር ነው። ሰው ነገ ወረርሽኝ ይመጣብኛል ብሎ ሲጨነቅ ክትባትን ይፈለስፋል ፤ ድርቅ ያጠቃኛል ብሎ ሲጨነቅ ዛፍ ይተክላል ፤ ወንዞችን ይንከባከባል ፤ ጦር ይመጣብኛል ብሎ ሲጨነቅ አዳዲስ መሳሪያዎችን ይፈለስፋል ፤ ጠንካራ ሆኖ በተጠንቀቅ ይጠባበቃል ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ያጠፋኛል ብሎ ሲጨነቅ አደጋው ከመምጣቱ በፊት ጥቆማ የሚያቀርብ መሳሪያ ይፈጥራል ። ስልጣኔ የጭንቀት ፍሬ ነው። ሰዎች በጉልበታቸውም ሆነ በእውቀታቸው መከራን ማስቀረት እንኳ ባይችሉ የመከራን ጉልበት መቀነስ እንደሚችሉ በታሪክ አይተናል። የእኛ ተክለሃይማኖታውያን የሚያቀርቡልን ግን “ እሱ ካመጣው አይቀርልህም “ የሚል ማዘናጊያ ነው ፤ ለነገሩ አባቶቻችን በክንፍ ከወፎች ጋር እንጅ በምድር ከሰዎች ጋር ስላልኖሩ የምድሩን ጠባይ ሊያውቁት አይችሉም። ተዘናግተው አስቀደሙን።
እንዲህ ወደ ነጥቡ ስትመጣ ጥሩ ነው ፤ ታዲያ ‘ስልጣኔ የጭንቀት ፍሬ ነው’ ለማለት ይኼ ሁሉ አላስፈላጊ ማጫፈሪያ ምን ባይ ነው? ... ጽሑፏን ተነባቢ ለማድረግ ነው? ... ነው ለየት ለማለት ያህል? ... አባት ለልጁ ‘የሰውን ጥረት በሙሉ ዋጋ የሚያሳጣ ምክር’ መከረው አልከን ግን ሳታውቀው ... አያይዘህ ከጥረት ጋራ እግዜርን መያዝ የሚበጅ መሆኑን ጠቆምከን(ምን ጠቆምከን ሰበከን እንጅ) ... እህ አባትዬው ‘የውስጥህን የሚያውቅ እግዚአብሔር ካልፈረደብህ ንብረትህ እየሰፋ ይሄዳል’ አለ አልከና ... ታዲያ ከየት ያመጣው ንብረት ነው የሚሰፋው? ... መቸም ንብረት እንደ ዝናም ከሰማይ አይወርድ ... ‘አባቶቻችን በክንፍ ከወፎች ጋር እንጅ በምድር ከሰዎች ጋር ስላልኖሩ የምድሩን ጠባይ ሊያውቁት አይችሉም’ ለተባለው ማጫፈሪያ ... በእውነት ጸሐፊውም አባቶቻችን ማለቱ ይገርማል ነው ምንድን ነው የሚባለው? ... እህ አንዳንዴም እኮ እናትን አባቴ ማን ነው? ብሎ መጠየቅ ደግ ነው? ... (ይኼኛው አስተያየቴ ታዲያ ሆዴን ቦርቀቅ አድርጌ ጸሓፊው ባለማወቅ አለው ብዬ ሳስብ ነው - አውቆ ተጠንቅቆ ካለውም ፤ ምንም አይደለም ... ጋጠወጥነት አዲስ አይደለም ... እንደ አንዳንዶቹ ‘የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች’ መብትም ነው) ... ጸሐፊው በዚህ አንቀፅ መጨረሻ ላይ ‘ተዘናግተው አስቀደሙን’ በማለቱ እንደለመደበት ፈገግ ሊያስብለን ከሆነ እተወው ነበር ( እንዲህ በግድ ግጠጡ እያለ የቀረበበትና ማስገደዱ አናዶኝ ያልገጠጥኩበት ጊዜ ጥቂት አይደለምና ) ፤ ግና ምናልባት አምርሮ ከሆነ ... እንዲህ ብለውስ፦ አስቀድመውን ከሆነም ወደታች ዝቅ ብለህ እንደምታመጣው ማለቃቀስ ምን ረብ አለው? ... ወገብህን ጠበቅ አድርገህ ዶማና አካፋህን ማንሳት ነው እንጅ ...
በአገራችን የተከሰቱ መከራዎች ከተፈጥሮ የፈለቁ በመሆናቸው መድህናቸውም ተፈጥሮአዊ ነው ፤ ረሃብን እንውሰድ ፤ ረሃብ ለሃገራችን አምስተኛ ወቅት ማለት ነው ፤ ክረምት ጥቢ በጋ በልግ አራቱ ወቅቶች ሲሆኑ ጠኔ አምስተኛ ወቅት ሆኖ ይከተላል። ዑደቱ ሳያቋርጥ ይመላለሳል። መከራን የእግዚአብሄር ፈቃድ ነው ብሎ የሚያምን ሕዝብ መከራን አስቀድሞ መከላከል የእግዜርን ፈቃድ መጻረር ይመስለዋል።እና ባንዱ ዘመን ድርቅ ይከሰታል። ድርቁ አስቀድሞ የቀንድ ከብቱን ይፈጃል ፤ ሰዎች ረሃቡ ሲጠናባቸው ፈረስና አህያ መብላት ይጀምራሉ ፤ (ከሙሴ ትዕዛዝ የጨጓራ ትዕዛዝ ያይላል) ባስ ሲልም ልጃቸውን የሚበሉ ወላጆች ይኖራሉ። ባጤ ሚኒሊክ ጊዜ አንዲት እናት ልጇን ከበላች በኋላ የሚከተለውን እንጉርጉሮ አይሉት ተረብ አወረደች።
ዳግመኛ ለመውጣት በሌላ መንገድ
ተመልሶ ገባ ልጅ በናቱ ሆድ
በዚህኛው ላይስ ልኮንንህ አልወድም ወንድሜ ... ምክንያቱስ፦ በእድሜዬ ወደ ብርሃን የሚያመጣን መልዕክት ሳያጨልሙ ማስተላለፍ የሚችሉ ጸሐፍትን ብዙም አላየሁም ... ሰው ደግሞ ካቅሙ በላይ አይጠየቅም ... ስለይህ በርታ ብለህ አጨልመው ... የጨለመውን ማጨለምማ መች ቸገረ ብለህ ...
እንዲህ ዓይነቱ መረን የለቀቀ መከራና እልቂት ሲደጋገም መሪዎች በመጀመሪያ የሚወስዱት እርምጃ የክተት ፀሎት ማወጅ ነው። ተፈጥሮ ግን ለፀሎት ደንታ የላትም ፤ “ ታግለህ ጣል አለበለዚያ የራስህ ጉዳይ “ በሚለው የተፈጥሮ ሕግ ውስጥ ኪሪያላይሶ ቦታ የለውም። ሰዎች በመቅደሳቸው በረንዳ ላይ ይሄኔ እኒያ የሕዝብ አለቆች የእግዜሩን መንገድ ለጊዜው ቸል ብለው ወደ ተፈጥሮ መንገድ ይዞራሉ ፤ በተፈጥሮ መንገድ ውስጥ አንበሳ ሲርበው ወደ አደን እንጅ ወደ ቤተ መቅደስ አይሄድም። ሮጥ ሮጥ ብሎ ሚዳቆን ሰብሮ ይመለሳል ፤ የኛ ነገስታትም የአንበሳውን አርአያ ተከትለው በእምነት የማይመስላቸውን ሀብታም ጎሳ ይጠሩና ከብቱን ነድተው ሲሳዩን ዘርፈው ይመለሳሉ። እነሱ ሞአ አንበሳ ሲሆኑ በርዕዮተ ዓለም የማይመስላቸውን ሕዝብ ሚዳቆ እንዲሆን ይፈርዱበታል። በዚህ ዓይነት ክፉ ቀንን በዝርፊያ ሲሳይ ይሻገሩታል። ኩነኔ አይፈሩም? የሚል ምዕመን ሊኖር ይችላል።
ይገርማችኋል ... ጸሐፊው የሃይል ጥቃት ደረሰበት ምናምን የሚል ነገር ሰምቼ እዝን አልኩኝና ... የሸገሩ ሰው ሰይፍሻ ከንፈሩን ሳይሆን ሃሳቡን ነው መሰንጠቅ ምናምን ሲል ጊዜና እርሱን ይዤ ስንጠቃ ስጀምር ፤ እግዜር ያቅልልህ ማለት ዳዳኝና ይህን አንቀፅ አይቼ ስላቅ እንዳይመስልብኝ ብዬ መለስኩት ... እህ እንዴት ያለ ነገር ነው? አሁን ለዚህ “ ታግለህ ጣል አለበለዚያ የራስህ ጉዳይ “ ደግሞ አይባል ነገር ... ለማንኛውም እንኳን እግዜር አተረፈው ... ሆ ... ሆ ነገር ከተፈጸመ በኋላ ጥቃቱ ልክ አልነበረም ... ተያዙ ... ተፈረደባቸው ምን ዋጋ ነበረው? ... ‘ተመስገን በል’ ብሏል ወዳጅህ ወዳጄ ...
ችግር አቆራምዶት ሌትና ቀን አዝኖ
ኩነኔስ መኖር ነው አለው በታች ሆኖ
የሚለው የከበደ ሚካኤል ግጥም የቀውጢ ሰዓት አቋማቸውን የሚወክል ይመስለኛል። የዓለም ታሪክ የሚያስተምረን ለስጋቸው የሚጨነቁ ሕዝቦች በልፅገው ለነፍሳቸው ብቻ የሚጨነቁ ሕዝቦችን መግዛት እንደሚችሉ ነው። የዳርዊን አገር ከአቡነ ተክለሃይማኖት አገር በላይ ተሳክቶለታል ፤ ዋናው ነገር ጠፈሩ የምናስበው ያክል የዋህ አለመሆኑን ማወቅ ነው ፤ ምድሪቱ ከፀሎታችን በላይ ላባችንን ፣ ከእንባችን ይልቅ ደማችንን ትጠይቃለች።
መምህሬ አለማወቅ ደፋር ያደርጋል ይሉ ነበር ... እንደዛ መሰለኝ ይኼኛውም ... ምክንያቱም ሁለቱንም ጥጎች አንድ ላይ ለማየት እና ለማወዳደር ፤ ሁለቱንም በደንብ ማወቅ ግድ ይላል። አይመስላችሁም? ... እህ ሃይማኖታውያን ለነፍሳቸው ብቻ የሚጨነቁ አይደሉማ ... ግን ግን ... ጸሐፊው ያኔ የኔታ ጋ ፊደል ሲቆጥር (እንግዲህ ዛሬ ከጻፈ በልጅነቱ የኔታ ጋ ሳይሄድ አይቀርም ብዬ ነው) ... እና ያኔ የእርሱ የፊደል ገበታ “ ሊሰራ የማይወድ ቢኖር አይብላ “ የሚል ነገር ጎኑና ጎኑ ላይ አልነበረም? ... ነው ፊደሏን ብቻ ነው ለቀም አድርጎ ወደ ቤቱ የተመለሰው? ... የቸገረ ነገር እኮ ነው እንግዳ ነገር የተገለጠለት ያህል ...
በዚህ ጽሐፍ ሳቢያ ከታዘብኳቸው፦
- ኃሳብን በኃሳብ ከመቃወም ዱላ የሚቀናቸው ብዙ ሰዎች አሁንም ድረስ መኖራቸውን። ...( ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ! ... እንደኔ አተያይ በተገቢው ሰዓት አካፋ አካፋ ሊባል ይገባዋል )
- በራስ አለመተማመንን የመሰለ ከባድ ፤ አቅልን የሚያስት በሽታ አለመኖሩን። ( በራሱ አመለካከት ፣ አተያይ ፣ አከሄድ ፣ እምነት ፣ ... ሙሉ እምነት ያለው ሰው ራሱን አስከብሮና የሌላውን አክብሮ ተቻችሎ ይኖራል እንጅ ፤ እርሱ ስለሚያምነው ነገር አዋጭነት ለማረጋገጥ ፤ የሌላውን መሳደብና ማንቃሸሽ አይገባውም። አልፎ ተርፎም የያዘው ሊያከስረው እንደሚችል በመስጋት አብሮ ተሰላፊ ጀሌ ፍለጋ ታች ላይ ማለት መብት ቢሆንም ትርፉ ድካም ይሆን እንደሆነ እንጅ ኪሳራውን የሚቀንስ አይሆንም )
- ለወትሮው ለቅድስት ቤ/ን ዘበኝነት ቆመናል ይሉን የነበሩ ፤ ስለ እንቶኔና እንትና የተደረገ ያልተደረገ ሲጽፉ የነበሩ አካላት ዝምታን መምረጣቸውን። ( እንደኔ አተያይ መጻፋቸውም ዝምታቸውም ያው ነው ፤ አይጠቅምምም አይጎዳምም ፤ የነርሱ መጻፍ ... እሰይ እንዲህ ልኩን አጉርሱት እንጅ የሚል ተሳቢ ቢያስደስት እንጅ ሌላ ዋስትና የሚሆነው ነገር አይኖርም ... የነርሱ አለመጻፍ ... ደርሰው በረባውም ባልረባውም እምቡር እምቡር ሲሉ አልነበር ፤ ምነው ታዲያ አሁን የሚል ትዝብት ቢያጭር እንጅ ሌላ ትርጉም አይኖረውም )
- ከወቅታዊ ብቃት ይልቅ የከረመ ስም ዋጋ ያለው መሆኑን። ( ጭፍን ካለ የአትንኩብን ለቅሶ ከመስማት ጀምሮ ፤ የጋዜጠኝነትን ሙያዊ ሥነ-ምግባር ሻሂ አጣጭ ጓደኝነት ቀድሞት ሲገኝ እስከማየት ድረስ ፣ ... )
Eyob G.
tromso, Norway
april 12, 2011