መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Tuesday, December 6, 2011

ሁሉም የሆነ ነው

ሁሉም የሆነ ነው

ሁልጊዜ አዲስ ነገር ምነው መወደዱ?
ሁሉም እያረጀ አይቀርም መሄዱ።

ሰሎሞን ብሎናል ደጉ ተመልካች
አዲስ ነገር የለም ከፀሐይ በታች።

ጄንጂስካን ቲሙርሌንግ አቲላ ቄሳር
ሻርልክ ናፖሊዮን ትልቁ እስክንድር
አልፎ አልፎ በተራ በቅደም ተከተል
ዓለምን በሙሉ ይዘው በመጠቅለል
በሰይፍ በጎራዴ ፍጥረት እያመሱ
በብዙ ጭካኔ ደም እያፈሰሱ
ይመስላቸው ነበር ሠርተው የፈጸሙ
ዳሩ ግን አልሆነም በከንቱ ደከሙ።

ዓለም ሳትለወጥ ባህልዋን ሳትረሳ
እስር ትገባለች ወዲያው ተመልሳ።

የታሪክን ጉዞ ያልተገነዘበ
ሁሉንም ያደንቃል እያጨበጨበ።

ለመጭው ሳያስብ ላላፊው ሳያዝን
በልማድ ይኖራል ጅል ሳያመዛዝን።

ብልህ ያስተውላል አይደናበርም
መሄድ መመለሱን አይጠራጠርም።


ጊዜ እየለወጠው የልማድን አዋጅ
ጠላት የነበሩት ይሆናሉ ወዳጅ።

እንዲሁም ቢመስለን ግራ መስሎ ለኛ
ፍየል ከነብር ጋር ይሆናል ጋደኛ።

ልበ ተላላ ሰው ዘላለም ይሞኛል
እስኪ ረግቶ ያለ ምን ነገር ይገኛል?

የተማመኑበት እየሆነ ፈራሽ
ሲፈጸም ይገኛል ያልታሰበው ጭራሽ።

ደካማ ይጠናል ኃይለኛ ሲዋረድ
ቡቃያ ይለማል ያፈራው ሲታጨድ።

ሰፊው ይቀነሳል ጠባቡ ሲሰፋ
ጨረቃ ታምራለች ጸሐይ ስትጠፋ።

ሀብታሙ ሲደኸይ ደሀ ሰው ይከብራል
አንዱ ሲደፈርስ አንደኛው ይጠራል።

ከእንቅልፉ ሲነቃ ቀድሞ የፈዘዘ
የሞቀው ይሄዳል እየቀዘቀዘ።

ትንሹም ትልቅ ነው ትልቁም ትንሽ
መጥፎም መልካም ነው መልካሙም ብላሽ።

እንደ ህልም ታይቶ ያልፋል እንደ ጥላ
የዚህ ዓለም ነገር ምንም የለው መላ።

ሁሉም ያለ ጊዜው ነውና አስቀያም
ዕውቀትም ጊዜ ነው ኃይልም አጋጣሚ።

ትልቅ ሰው ሲቀበር ሕጻን ይወለዳል
አንዱ ሲመሰረት አንደኛው ይናዳል።

ሳይተጓጐሉ እንበለ ፍጻሜ
ይፈራረቃሉ ጠፍና ልምላሜ።

እንዲህ ከሆነማ የፍጥረት ልማዱ
ሰዎች ተቀበሉት ብትወዱም ባትወዱ።

ጥንትም ወደፊትም ዛሬም በዚህ ዓለም
ሁሉም የሆነ ነው አዲስ ነገር የለም።

የዕውቀት ብልጭታ
ገፅ ፷፪
እጅጉን መወደድና መከበር የሚገባቸው ዶ/ር ከበደ ሚካኤል

No comments:

Post a Comment