መቅድም
ከዚህ አጭር ሀተታ በታች የምትመለከቱት ጽሑፍ ፤ በኢትዮጵያ ሥነፅሑፍ ታሪክ ውስጥ ገናና ከሆኑት ደራሲያን መካከል አንዱ የሆኑት ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል የዕውቀት ብልጭታ በተሰኘ መጽሐፋቸው መግቢያ መቅድም አድርገው የጻፉት ነው። የተከበሩ ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ጥቅምት ፳፫‚ ፲፱፻፱ የተወለዱ ሲሆን ፤ የቤተክህነትን ትምህርት ካገባደዱ በኋላ በአሊያንስ ፍራንሴዝና በላዛሪስት ሚስዮን ዘመናዊ ትምህርትን ተከታትለዋል። የግሪክን ፣ የእንግሊዝን ፣ የፈረንሳይን ፣ የጀርመንን ፣ የሩስያንና የጣልያንን በርካታ መጻሕፍት ከመረመሩም በኋላ ሃያ ስድስት መጻሕፍትን ለወገኖቻቸው ያበረከቱ ሲሆን ፤ በድርሰቶቻቸው ውስጥ የሚታዩት የሀሳብ አገላለጾች ፣ ቃላትና ዘይቤዎችም ኋላ ለመጡ ደራሲያን የነበራቸው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ይህንንም፥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለድንቅ ተግባራቸው በ፲፱፻፺ ዓም የክብር ዶክተርነት ክብርን በሰጠበት ወቅት “ … በተለይ ከ፲፱፻፶ዎቹ ወዲህ የተነሱ በርካታ ደራሲያን ፤ የርሳቸውን ድርሰቶች አንብበው ፣ በርሳቸው ድርሰቶች ሥነጽሑፍን አውቀውና አጣጥመው ደራሲ ሊሆኑ በቅተዋል።” በማለት ምስክሩን ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪ እኒህ ታላቅ ደራሲ ትኩረታቸውን ሕጻናትና ልጆች ላይ ያደረጉ ፤ ግብረ ገብ የሚያስተምሩ ፣ ስለወገንና ሀገር ፍቅር የሚሰብኩ እና የዕውቀትና የሥራ ጠቀሜታን አጉልተው የሚያሳዩ አያሌ የሥነጽሑፍ ሥራዎችን አበርክተዋል።
ይህን መቅድም ባነበብሁት ጊዜ ሁሉ ፤ ለሕጻናቱ ስሱ መሆናቸው … ለሕጻናቱ ያላቸው ከበሬታ … ባልደከሙበት እንዳያመሰግኑዋቸው ሕጻናቱን ግድ የሚሉበት ሞራል … አልፎ ተርፎም ክብርና ምስጋና ለሚገባው ክብርና ምስጋናን እንዲሰጡ ለሕጻናቱ ግብረ ገብ የሚያስተምሩበት አግባብ … እንዲሁም ለቀጣይ ትውልድ ጠቃሚ የሆነ ሥራን ስለመስራት ለሕጻናቱ ኃላፊነትን የሚሰብኩበት መንገድ ልቤን አንዳች ሀሴት ይሞላዋል … እነሆ፥ እኔን ደስ ያሰኘኛልና እናንተንም ደስ ቢያሰኛችሁ ጻፍኩላችሁ …. እነሆ፥ እኔን መደነቅ ውስጥ ይጥለኛልና ቢያስደንቃችሁ ጻፍኩላችሁ … እነሆ፥ የዛሬን በትላንት ሳየው ይቆጨኛልና ቢቆጫችሁ ጻፍኩላችሁ … እነሆ በደራሲው አምሳል ለሕጻናት ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን መስራት ቢከብደን በስራዎቻቸው ሕጻናቶቻችንን ማስተማር አይከብደንምና ስለማስታወስ ጻፍኩላችሁ ….
“መቅድም፡
ተርቦ ለመጣ ሰው ባዶ መሶብ ቢያቀርቡለት በውስጡ እንጀራና ወጥ ካላገኘበት ሊጠግብ አይችልም ፤ እናንተም በየትምህርት ቤቱ ያላችሁ ሕጻናት እንደዚሁ መጻሕፍት ከሌሉ የትምህርት ቤት ብቻ ቢከፈትላችሁ የትምህርቱን እንጀራ ልትመገቡ አትችሉም። ይህንንም ስላልሁ በትምህርት ቤት ውስጥ በውጭ አገር ቋንቋ የተጻፉ በየዓይነቱ ትምህርት የምታገኙባቸው መጻሕፍት ተሰናድተው እንደሚቀርቡላችሁ አውቃለሁ ፤ ግን ሕጻን የባዕድ ቋንቋ ተምሮ በውስጡ ያለውን ምሥጢር ለመረዳት እስኪችል ድረስ ያለበት ድካም እኔም እንደ እናንተ ሕጻን በነበርሁ ጊዜ ስለደረሰብኝ ይህ ድካም እንዲቃለልላችሁ ባለኝ አቅም ስረዳችሁ በጣም ደስ ይለኛል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሁለት ዋኖች ነገሮች ተከትያለሁ፦
አንደኛው በተረትና በጨዋታ አነጋገር ሆኖ የምታገኙት የሙቀትንና የብርድን ፤ የመጥፎ አየርንና የነፋስን ባሕርይ በአጭሩ የሚያስረዳችሁ ለጥበብ (ሳይንስ) ትምህርት መሰናጃ የሚሆናችሁ ንባብ ነው። ይህንንም አብዛኛውን ያገኘሁት ቶልስቶኢ ከሚባለው ከትልቁ የመስኮብ ደራሲ መጽሐፍ ውስጥ ነው ፤ እሱም ትልልቅ መጻሕፍት የጻፈ ዐዋቂ ሆኖ ሳለ ለሕጻናት የሚጠቅም ነገር ላሰናዳ ብሎ አስቦ በመድከሙ በዓለም ላይ ያሉ በእሱ መጽሐፍ የሚማሩ ብዙ ሕጻናት አመስግነውታልና እናንተም አመስግኑት። ከእሱ ያገኘኋቸውን ሁሉ እመጨረሻው ላይ (ሌ፡ቶ) የሚል ምልክት አድርጌባቸዋለሁ ይህም ሌዎን ቶልስቶኢ ማለት ነው።
ሁለተኛውም በአለፉት መጻሕፍቶቼ የሚያጫውቱና የሚያስቁ ሆነው በውስጣቸው ትምህርት ያለው ምሥጢር የሚገኝባቸው ተረቶች በግጥምና በስድ ንባብ እያደረግሁ አሰናድቼላችሁ ነበር ፤ በዚህ በአሁኑ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ከፍ ካለ የትምህርት ደረጃ ስትደርሱ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከምታገኙዋቸው ፤ በየዘመኑ ተፈጥረው ከነበሩት ታላላቆች ሰዎች ጋር የሚያስተዋውቋችሁ ተረቶች ጽፌላችኋለሁ። በእነዚህም ተረቶች ውስጥ ካምቢዝ ፣ ዲዎጋን ፣ ጄንጂስካን የሚባሉና እነሱንም የመሰሉ ሰዎች ታገኛላችሁ። ወደፊት በዓለም ላይ ትልልቅ ሥራ የሠሩ ስለሆኑ ካሁኑ ጀምሮ ስማቸውን ብታውቋቸውና ከባሕሪያቸውም ጥቂት ነገር ብታውቁ ይጠቅማችኋል።
በጣም ደግሞ አደራ የምላችሁ የውጭ አገር ቋንቋ ከተማራችሁ በኋላ ስጦታችሁ በሚያደላበት ዕውቀት እየደከማችሁበት በውስጡ የምታገኙትን ፍሬ ነገር እያጣራችሁ ወደ አማርኛ ቋንቋ እንድትገለብጡትና ከናንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆች አውርሳችሁ ቋንቋችሁን እንድታበለጥጉበት ነው።
የባዕድ ቋንቋ በወንዝ ፣ በምንጭ ወይም በጉድጓድ ውኃ መመሰሉን አትርሱ። ሰው ውኃ ወደ አለበት ስፍራ ሲሄድ በእንስራ ወይም በመቅጃ አምጥቶ ለቤተሰቦቹ ካልሰጠ ለራሱ ብቻ ጠጥቶ ቢመለስ ድካሙ ፍሬ ሳይሰጥ መካን ሆኖ ይቀራል ፤ የውጭ አገር ቋንቋ ተምሮ ብዙ መጻሕፍት ወደ አገሩ ቋንቋ የሚተረጉም ሰው ግን የወንዙን ውኃ በቦይ መልሶ ድርቀት የጎዳውን የአባቱን ርስት እያጠጣ በሚያለማ ሰው ይመሰላል። ከሌላው ቋንቋ ቀድተው ያመጡትን ለአገራቸው ቋንቋ ማሰልጠኛ ያደርጉታል እንጅ በሰው ቋንቋ ብቻ የሰለጠኑ ሕዝቦች አታገኙም። የውጭ አገር ቋንቋ ብቻውን ቢስፋፋ የሚጠቅም እንዳይመስላችሁ ፤ ከባዕድ እየጎረስህ ወደ ዘመድህ ዋጥ የሚባለውን ተረት አስቡ።”
No comments:
Post a Comment