ትንቢተ ዮናስ
ምዕራፍ ፩
በሕዝብዋ መካከል ፤ ዓመፅ ስለ ጸና
በጣም ተቆጥቼ ፤ አዝኛለሁና
ይህን ለነነዌ ፤ንገራት በአዋጅ
አለና ለዮናስ ፤ ለአሚታይ ልጅ
እግዚአብሔር አዘዘው ፤ እንዲሄድ በቶሎ
ዮናስ እምቢተኛው ፤ አሰበ ኮብልሎ
ከአምላክ ተደብቆ ፤ አምልጦ ሊጠፋ
ወደ ተርሴስ ሊጓዝ ፤ ሄደ ወደ ያፋ።
ዋጋ ከፈለና ፤ በመርከብ ተሳፍሮ
እያጉረመረመ ፤ ባሕሩን ተሻግሮ
ዮናስ ተደብቆ ፤ ሲሄድ በግስገሳ
ከእግዚአብሔር ተልኮ ፤ ማዕበል ተነሳ
ታላቅ ሞገድ ሆኖ ፤ ባሕሩ ተቆጣ
መርከበኞች ፈሩ ፤ ትልቅ ሽብር መጣ
መርከቡ እንዲቀልለው ፤ እናድርግ እያሉ
አንስተው ብዙ እቃ ፤ ወደ ባሕር ጣሉ
ባሕሩም ባሰበት ፤ በጣም ተናወጠ
መርከቡ መሰለ ፤ የተገለበጠ።
ሰው ሁሉ ተነሳ ፤ ጸሎት ለማድረስ
ይኽ ሁሉ ሲሆን ፤ ተኝቷል ዮናስ
ወደ ዮናስ ሄዶ ፤ የመርከቡ አለቃ
ቀሰቀሰውና ፤ ከእንቅልፉ ሲነቃ
እግዜር እንዲያድነን ፤ ከዚህ ክፉ ጥፋት
ተነስ ጸልይ አለው ፤ ይብቃህ ማንቀላፋት።
በመርከብ ውስጥ ያሉ ፤ ሰዎች ተሰባስበው
ተመካከሩና ፤ በነገሩ አስበው
አለ ኃጢአት ሰርቶ ፤ ከእኛ ጋር የመጣ
ለይተን ለማወቅ ፤ እንጣጣል ዕጣ
አለዚያ አንድንም ፤ ስለተባባሉ
ተሰባሰቡና ፤ ዕጣ ቢጣጣሉ
እውነትም እንዳሉት ፤ አጥፊው ሰው ታወቀ
በእምቢተኛው ነቢይ ፤ በዮናስ ወደቀ።
ዮናስ ተረዳና ፤ እጁ እንደተያዘ
ያጠፋውን ጥፋት ፤ ገልጦ ተናዘዘ።
ምነው ባትመጣ ፤ ተጣልተህ ከጌታ
እየው መርከባችን ፤ እንደሚንገላታ
ቁጣው እንዲታገስ ፤ ለማግኘት ጸጥታ
በል አንተው ፍረደን ፤ ምን ይበጃል ቢሉ
ዮናስ መለሰና ፤ እዚህ ያለ ሁሉ
ስለምን ይጠፋል ፤ በኔ የተነሳ
ወደ ባሕር ጣሉኝ ፤ አለብኝ አበሳ።
ተመልከቱ እነሆ ፤ ሥራውን አወቀ
ጥፋቱን ገለጠ ፤ ይኸው መች ደበቀ
እሱው ከፈረደ ፤ መልሶ በራሱ
ምን እናድርግ ብለው ፤ ሊጥሉት ተነሱ
ከደሙ አንጻን ሲሉ ፤ ለእግዜር አመልክተው
ወደ ባሕር ጣሉት ፤ ዮናስን አውጥተው።
በዮናስ ላይ ኖሮ ፤ የመጣው ይህ መዓት
ባሕሩ ጸጥ አለ ፤ ልክ በዚያው ሰዓት።