መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Friday, July 30, 2010

" እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን ፍፁሙንም መርምሩ " ሮሜ 12 ፦ 2

" እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን ፍፁሙንም መርምሩ " ሮሜ 12 ፦ 2

በስመ ሥላሴ አሜን።

ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ።

" እያንዳንዳችን ...
  ቤታችንን ..
  ብንጠርግ ... ብናፀዳ
  አዲስ አበባችን ... ምን ያህል በፀዳ "
*  * * * * * * * * * * *
የማይመስል ነገር ... የማይሆን ግርግር
             ...  የቆሻሻ ክምር ...
'ራሱ ቆሽሾ ሌላውን ሊያቆሽሽ ባሰፈሰፈ አገር።

ይህችን ግጥም ቢጤ ፦ በአንድ ወቅት በመዲናችን በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የክፍለሃገር ከተሞች ሰሞነኛ አጀንዳ ሆኖ ለሰነበተና ለቅፅበት ታይቶ ለጠፋ የፅዳት ዘመቻ ነበር የሞነጫጨርኳት ...

በወቅቱ የዘመቻ ባህሪይ ከሆነ ትኩሳትና ስሜታዊነት የተነሳ የከተሞችን ገፅታ በመቀየር ሒደት የተለያዩ እና ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራት ሲሰሩ እንደነበረ የብዙዎቻችን ትውስታ ነው። ... የሆኖ ሆኖ ወደ ዘመቻ የተገባው የህዝቡን አመለካከት በማሳደግ በኩል በቂ ስራ ሳይሰራ በመሆኑ የተጠበቀው አዲስ አበባን ፅዱና አረንጓዴ የማድረግ ግብ ከፍፃሜ ሳይደርስ ... የአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ለዚህም በአዲስ አበባ ባምቢስ እና መገናኛ ድልድይ አካባቢየሚገኙ ቦታዎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል ... አምረውና ተውበው ለህዝብ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አውርተን ሳንጨርስ ወደቀደመ የቆሻሻ መነኻሪያነታቸው ተመልሰዋልና ... እንዲህም ማለቴ በጊዜው የነበረውን መነሳሳት ፤ የዚህንም መነሳሳት ግምባር ቀደም ተዋናይ ፦ የአርቲስት ጋሽ አበራ ሞላን ዋጋ ለማሳነስ ( ቸርችል ቪውን የመሰሉ ምሳሌ የሆኑና ይበል የሚያሰኙ ስራዎች የዚህ መነሳሳት እሳቤ ውጤቶች ናቸውና )  ሳይሆን የህዝቡ የአመለካከት ለውጥ ዘመቻውን ሊቀድመው ይገባ ነበር ለማለት ነው። ...

Thursday, July 22, 2010

ስብሐት ይሁን

ስብሐት ይሁን

ለ ... ጭንቀት
ለ ... ርሀብና ለ ... ጥማት
ለ ... ድካም
ለ ... ስቃይና ለ ... ህማም
ብቻ ...
ቀድሞ ለ ... 'ሚሆን
ችጋር ...
ስብሐት ይሁን።
እንዲያ ባይሆን ሲጀመር
ደስታ ፤ ሐሴት ... 'ሚባል ነገር
እንዴት ይገባን ነበር?



21/12/98
ይርጋለም

Wednesday, July 21, 2010

" በእምነት ስላልተዋሃደ ... አልጠቀማቸውም " ዕብ 4፦2

" በእምነት ስላልተዋሃደ ... አልጠቀማቸውም " ዕብ 4፦2

በስመ ሥላሴ አሜን።

በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ከእኔ ከወንድማችሁ ፦ የክርስቶስ ኢየሱስ የመንግስቱ ወራሾች ትሆኑ ዘንድ ለተጠራችሁ ለናንተ ፦ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ፤ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
ወንድሞች ሆይ ፦ የነፍሳችንን ድኅነት ፤ የልጅነትን ክብር ፤ ተስፋ ስለማድረግ ምክንያት በቤተክርስቲያን ጥላ ስር በእምነት የምንኖር ነንና እራሳችንን ከእግዚአብሔር ቤት ሕግና ሥርዓት በታች እናስገዛለን ፤ ታዲያ ምንም እንኳን በልቦናችን ያለው ይህ የእግዚአብሔር ሕግ መልካም ቢሆንም (ሮሜ 7 ፦ 22) ከሥጋችን ደካማነት ፣ ከዲያቢሎስም ውጊያ የተነሳ የኃጢአትን ሕግ እንመለከታለን። እንዲህም ስለሆነ እባብ ሔዋንን በተንኮሉ እንዳሳታት ለሥጋ በመድከማችን ምክንያት አሳባችንና ፈቃዳችን ከክርስቶስ የዋህነትና ንፅህና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እሰጋለሁ። ... ወዲህም ደግሞ " እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን " (ሮሜ 8 ፦ 28) ስለተባለው የተስፋ ቃል ከስጋቴ አርፋለሁ ... ቢሆንም ግና አሁንም መልሼ እሰጋለሁ ... እግዚአብሔርን ከሚወዱት ከምርጦቹ መካከል አንሆን ይሆን ብዬ ... ምክንያቱስ ፦ እርሱን የሚወዱ ፍለጋውን ይከተላሉ ተብሏልና ... ታዲያ ስንቶቻችን ጎዳናውን ተከትለናል? ... እግዚአብሔርን መውደዳችንስ ወዴት አለ? ... እንዴትስ እየገለፅነው ነው? ...

Tuesday, July 20, 2010

ያልታደለችዋ ዛፍ

ያልታደለችዋ ዛፍ

ባንድ ወቅት የአንድ ዛፍ
ግንዱ ከቅርንጫፍ
ቅርንጫፍም ባቅሙ ከሌላ ቅርንጫፍ
ተጣሉ ይባላል ፈልገው ትርፋ ትርፍ።

ታዲያ በዚህ ነገር ስሩ እጅግ አዝኖ
ሊሸመግል ገባ በመካከል ሆኖ

ከዚያም ሽማግሌው ሁሉንም ቃኘና
እርቁን አስጀመረ እንደዚህ አለና
ስሙ አካላቶቼ ነገሬን አድምጡ
ሕይወታችን ሆኗል ከድጥ ወደማጡ።
ምንም እንኳ ምግቡ ብዙ ቢትረፈረፍ
ተፈጥሮ ቢያድለን ሁሉን ነገር በገፍ
ያው እንደምታውቁት እኔ አባታችሁ
በጎርፍ በፀሀዩ ደካማ ሆኛለሁ።
እንዲያም እንኳ ቢሆን እንደምንም ብዬ
ቁሩንም ጎርፉንም ንዳዱንም ችዬ
ለኑሮ የሚሆን ምግብ ፈላልጌ
እየላክሁላችሁ በግንድ አድርጌ
እየኖርን ነበር በሰላም ተዋደን
ችግሩን ስቃዩን በአንድነት ችለን።
ሰሞኑን ግን እኔን አልጥምህ ብሎኛል
ጠባችሁ ከባብዶ ገዛዝፎ ታይቶኛል።

በማለት አቅንቶ ግንዱን ተመልክቶ
የብዙ ቅርንጫፍ ክስን ሁሉ አይቶ
እንዲህ ሲል ወቀሰው በሀዘን ተጎድቶ

Saturday, July 17, 2010

ተረት ተረት

ተረት ተረት

*********
ድ***ሮ***በጥንት ጊዜ ነው አሉ
የዱር አራዊት የተባሉ
በ***ሙ***ሉ
በየወገን በየወገናቸው
በየጫካ በየስርቻቸው
አስተዳዳሪ፤
መሪ፤
የሚሉት ኖሯቸው
ይኖሩ ነበር ደልቷቸው
***ተመችቷቸው።
*************
ከዚያም ሲኖሩ ፣ ሲኖሩ ፣ ሲኖሩ
**************
ከእለታት በአንድ ቀን
አንበሳ የሚሉት ወገን
ከነበረበት ፤ ካለበት ... እምቡር ብሎ ወጥቶ
አራዊቱን ሁሉ በክርኑ እጅ ... አሰጥቶ
ራሱ ሿሚ
እሱው ተሿሚ
ሆኖ አስተዳዳሪ ... የዱር አራዊቱ ሁሉ መሪ
***************
የራሱን የኑሮ ድሎት
የራሱን መንደር ምቹነት
የናንተም ነው እያለ ... እየለፈፈ
ደንቁሮ እያደነቆረ ... ዘመናትን አሳለፈ።
****************
ታዲያ እነርሱም ...
ብ ... ዙ ... በጣም ብዙ ግፍ እየቆጠሩ
ባንበሳው አገዛዝ እየተማረሩ
ብዙ ዘመን ኖሩ።
***************
ጥያቁም ሲያነሱ
... ስለሚደቆሱ
ጨከን ... ጨከን ያሉ
ካያ አንበሳ ይርቃሉ
በሌላ ጫካ ፤ በሌላ ስርቻ
... የስደትን ኑሮ ይገፋሉ።
ለመጨከን ያልታደሉ
በየወገናቸው ያንሾካሹካሉ
ያንሾካሹካሉ ... ያንሾካሹካሉ
ድንገት ጮክ ሲሉ ... ይኮረኮማሉ
ተመልሰው ያንሾካሹካሉ
... ይደቆሳሉ።
ያንሾካሹካሉ ፤ ያንሾካሹካሉ
... ያንሾካሹካሉ ...



02/05/98
አ.አ.

Wednesday, July 7, 2010

አንተ 'ወንበር' ... እባክህ ተናገር

አንተ 'ወንበር' ... እባክህ ተናገር

አንተ የኛ ቤት ... ትልቅ 'ወንበር'
እስኪ ተጠየቅ ... በል ተናገር
* * *
አንተን የነካህ ... በ...ሙ...ሉ
ተቀያይሮና ... ተለዋውጦ አመሉ
ጨክን ጨክን ... የሚለዉን
ፍርድ አጓድል ... ያሰኘውን
ንገረን እስኪ ... በሽታውን
* * *
በበፊቱ ወንበር ... መቆርቆር
የኖረው ሁሉ ... ሲያማርር
ቀን ሲወጣ ... እድል ሲያምር
ሲፈናጠጥ ... ያንተን መንበር
የቀየረውን ... በል ተናገር
* * *
ሞገስህ ነው? ድሎትህ?
ሙቀትህ ነው? ቁመትህ?
እባክህ አንተ 'ወንበር'
ጨንቆናልና ተናገር።


12/01/98
ዲላ