መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Sunday, January 29, 2012

ትምህርተ ሃይማኖት በጸሎተ ሃይማኖት


በስመአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ትምህርተ ሃይማኖት በጸሎተ ሃይማኖት

ውድ አንባቢያን ወገኖቼ ሆይ የሰው ልጅ በዓመፅ በእምቢተኝነት በቸልተኝነት በዝንጋኤ በግዴለሽነት ወይም በልዩ ልዩ ዓለማዊና ምድራዊ አኗኗር በተለይም አእምሮን በሚያሳጣ በክፉ ልማድ ተጠምዶ በልቡናው ያለውን የእግዚአብሔር ዕውቀት ወይም እምነት ካልተወ በቀር የሃይማኖት ስሜትና አሳብ ፈፅሞ አያጣም ከዚህም ስሜቱና አሳቡ የተነሳ በፍኖተ አእምሮ በእግረ ልቡና በመመራት ይልቁንም በመጀመሪያ በቤተ እስራኤል ቀጥሎም በቤተ ክርስቲያን በሆነው የእግዚአብሔር መገለጥ ፈጣሪውን ወደማመን ይደርሳል ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንም ይህን አስቀድሞ በትንቢት በታሪክና በምሳሌ ኋላም በአማናዊነትና በፍጹምነት የሆነውን መገለጥ ለሁሉም ወገኖች ታስተምራለች አስተምህሮዋም በጸሎተ ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ቢያውቁት ቢረዱትና ጸንተው ቢኖሩበት የኅሊና ሰላምን የሚሰጥና ደኅንነትን የሚያስገኝ  ነው

ጸሎተ ሃይማኖት ታሪካዊ አነሣሡ ምንም እንኳ መናፍቃንን ለመለየትና ምእመናንንም በትክክለኛው ሃይማኖት እንዲጸኑ ለማድረግ ታስቦ በጉባኤ ኒቂያ (325 ዓ.ም.) እና በጉባኤ ቁስጥንጥንያ (381 ዓ.ም.) የተወሰነ ቀኖና (ሕገ) ሃይማኖት ቢሆንም የትምህርቱ ይዘት ግን ከጥንት ጀምሮ በጌታና በሐዋርያት ትምህርት ውስጥ የነበረ ነው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደ ዛሬው ሳይከፋፈሉና ሳይወጋገዙ በኅብረትና በአንድነት በሚሰሩበት ጊዜ የነበሩ መንፈሳውያን የሃይማኖት መሪዎችና ሊቃውንት አባቶች ይህን ጸሎተ ሃይማኖት ከቅዱሳን መጻሕፍት አውጣጥተው በ12 ክፍሎች ከፍለው በማዘጋጀት የክርስትና መሠረተ እምነት ሆኖ እንዲሠራበት በውሳኔአቸው ለአብያተ ክርስቲያናትና ለምእመናን ሁሉ አስታውቀዋል አውጀዋል  

ከዚህ ቀጥሎ አሥራ ሁለቱን የጸሎተ ሃይማኖት አንቀጾች በመከተል ለየኃይለ ቃላቱ ከቅዱስ መጽሐፍ የሚመስላቸውንና የሚስማማቸውን ጥቅስ ለአብነት በማምጣት ለማሣየት ተሞክሯል  

መልካም ንባብ …

1.    ነአምን በአሐዱ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኩሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ/ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን
1.1.     ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታይና የማይታየውን በፈጠረ … (ሥነ ፍጥረት)
v  «በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ምድርም ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም … » ዘፍ 1 1-28
v  «አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ ምድርንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ፈጥረሃል …» ነህ 9 1-6
v  «ሁሉም በእርሱ ሆነ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም» ዮሐ 1 3
1.2.  በአንድ አምላክ …
v  «ያለና የሚኖር እኔ ነኝ» ዘጸ 3 14
v  «እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው» ዘዳ 6 4
v  «ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሰራ በሁሉም የሚኖር የሁሉ አባት እግዚአብሔር አንድ ነው…» ኤፌ 4 6
1.3.  በእግዚአብሔር አብ … (ምሥጢረ ሥላሴ)
v  «እኔ ከእግዚአብሔር አብ ወጥቼ መጥቻለሁና» ዮሐ 8 42
v  «እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል» ዮሐ 15 26
v  «የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ …» 1ዮሐ 3 1

ማስታወሻ እግዚአብሔር አብ (አባት) ብቻውን አብ (አባት) እንደማይባልና ከእርሱ ጋር የባሕርይ ልጁ ወልድ ዋሕድ እንዳለ መረዳት በተጨማሪም ከእርሳቸው ጋር ደግሞ የባሕርይ ሕይወታቸው እስትንፋሳቸው መንፈስቅዱስ እንዳለ ማስተዋል ይገባል
1.4.  እናምናለን …
v  «እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው» ዕብ 11 1
v  «ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም … ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ (እንደነበረ እንደሚኖር) ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል» ዕብ 11 6
v  «እምነት መሠረት ነች ሌሎቹ ግርግዳና ጣራ ናቸው» ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ