በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የመስጠትና የመቀበል ሥሌት
የሰውን ልጅ የኑሮ ዑደት ፤ ሚዛን በመጠበቅ ረገድ የመስጠትና የመቀበልን ያህል ሚና ያለው አንዳች ነገር ፈልጎ ማግኘት እጅጉን አዳጋች ነው። የሥነ-ፍጥረትን አሰራር ፣ አካሄድ ፣ እና አኗኗር በማስተዋል ለተመለከተ ሰው ፤ የዚህ ዓለም ፈጣሪና መጋቢ እግዚአብሔር አምላክ ፤ ዓለሙን በዚህ የመስጠትና የመቀበል ሥሌት እንዳፀናው ለመረዳት አይቸግርም ፤ ለአብነት እንኳ የሰውን ልጅ የአተነፋፈስ ሥርዓት ብንመለከት ፤ ወደ ውስጥ የምናስገባውን ኦክስጅን ለመቀበል ምንም ያገለገለና የተቃጠለ ብንለው ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን መስጠታችን ( ማስወጣታችን ) ድርድር የማያስፈልገው ነው ፤ ባንጻሩም ዕፅዋትና አዝርዕትም ቢሆኑ ፤ በፋንታቸው ምግባቸውን ለማዘጋጀት እንደ አንድ ግብዓት የሚያስፈልጋቸውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ለመቀበል ኦክስጅንን መስጠት ይኖርባቸዋል። ... ይኸስ ባይሆን ኖሮ ሁሉን ሊያደርግ የሚቻለው ፈጣሪ ፤ በየጊዜው ፦ በየዘመኑ ለሚኖሩ ሰዎች እና ዕፅዋት እንደ ልካቸው ( ብዛታቸው ) የሚያስፈልጋቸውን ፤ ለዚህን ያህል ሰው ይህንን ያህል ኦክስጅን ፣ ይህንንም ያህል ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ ፤ ለዚህን ያህል ዕፅዋትም ... እያለ እየሰፈረ እና እየለካ ባዘጋጀ ነበር ፤ ነገር ግን ፈቃዱ ለአንዱ መኖር የሌላውን ህልውና ግድ የሚል ፤ አንዱ እንዲቀበል ለሌላው መስጠትን ቅድመ ሁኔታ ያደረገ ፤ አንዱ ለሌላው ፣ ሌላውም በሌላው ላይ ያለውን ተደጋግፎት የሚጠይቅ ፤ ... ነው።
በቅዱስ መጽሐፍ ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመስጠትንና የመቀበልን ሥሌት በተለያዩ ሀገራት ለተለያዩ ሰዎች እንዳስተማረና ይኼውም ትምህርቱ የዘለቃቸውና የተረዳቸው የተጠቀሙበትም በፊልጵስዩስ የነበሩት ሰዎች ብቻ እንደነበሩ ተጠቅሶ አለ። " ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተክርስቲያን በመስጠትም ቢሆን በመቀበል ከእኔ ጋር እንዳልተባበሩ እናንተ ታውቃላችሁ " ፊሊ 4 ፦ 15 .... እኒህ በጥንቷ ግሪክ ሰሜናዊ ጫፍ ፤ በመቄዶንያ አውራጃ ትገኝ በነበረችው ፊልጵስዩስ የነበሩ ሰዎች ይህን የመሰለውን ምስክርነት ከታላቁ ሐዋርያ ያገኙት ፤ ሐዋርያው በሮም ሀገር የቁም እስረኛ በነበረበት ወቅት ልከውለት ሥለነበር አስተዋፅዖ ምክንያት ነው። ... ለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከተላከለት አስተዋፅዖ ላገኘው ጥቅም ምስጋና ፤ ይኸውም አስተዋፅዖዋቸው እንዳይቋረጥበት ሰግቶ ይህንን ተናገረን? ... እንዲያውም! ... ይልቁንስ ከበጎ ሀሳባቸው የተነሳ ሁሉ ካለው አምላክ ዘንድ በረከትን እንደሚያገኙ አስቦ ተናገራቸው እንጅ ፤ ይኼውም " ይህንም የማነሣሣው ስጦታችሁን ፈልጌ አይደለም ፤ በእናንተ ላይ የጽድቅ ፍሬ ይበዛ ዘንድ ፈልጌ ነው እንጅ " ፊል 4 ፦ 17 ባለው ይታወቃል። ... በዚህ ዘመንም ሰዎች በተለያዬ ሁኔታና መንገድ በተለያዩ ምክንያቶች ተነሳስተውና ተገፋፍተው አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። ... ለመሆኑ ከሚሰጡት መካከል ... ስንቶቹ ደጅ ተጠንተው ሰጡ? ... ስንቶቹስ ይህን አደረጉ ፤ ይህንን ደግሞ ሰጡ ፤ አጨብጭቡላቸው ፤ እልል በሉላቸው መባልን ሽተውና ስማቸው በአደባባይ እንዲጠራ ፈልገው ሰጡ? ... ስንቶቹስ ባለማስተዋልና በክፉ ብልጣብልጥነት ፤ ዘርዝረው የበተኗት አንድ ብር አንድ ሽህ እንድትወልድ ሰጡ? ... ስንቶቹስ እንደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ባለ መልካምነት ፤ የሚሰጡት ገንዘብ እግዚአብሔርን ሊደጉመው ፤ የሚያመጡት እጣን ከመዐዛው መልካምነት የተነሳ ሊያሸተው ፤ የሚያገቡት ጧፍም ጨለማውን ሊያርቅለት ሳይሆን ፤ የሰጡትን ከሰጡበት በጎ ኅሊና ( ሀሳብ ) የተነሳ የእግዚአብሔርን በረከት ሽተው ሰጡ? ... ቤት ይቁጠራቸው። ... የመስጠትና የመቀበል ሥሌቱ የገባቸው የፊልጵስዩስ ሰዎችስ ' እኛ በጫና ያይደለ በውድ ያለንን ደስ እያለን እንሰጣለን ፤ አንተ ደግሞ ለእኛ ምን ፤ መቼ እንደሚያስፈልገን ታውቃለህ ፤ በጊዜህም ታደርግልናለህ ' በሚል እምነት ሰጡ።
ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት ለእግዚአብሔር ታቦት ማደሪያ ቤተ-መቅደስ ሊሰራ መሻቱ በሆነና ሥለዚህም ነገር የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጠየቀ ጊዜ ፤ እግዚአብሔር አምላክ በነብዩ በናታን አድሮ በእርሱ እጅ ብዙ ደም ስለፈሰሰ ፤ ቤተ-መቅደሱን ልጁ ሰሎሞን እንጅ እርሱ እንደማይሰራ ነገር ግን ለእርሱ የሚያስፈልገውን እንዲያከማችለት በተናገረው መሰረት ፤ የእግዚአብሔር ቤተ-መቅደስ ይሰራበት ዘንድ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከሰበሰበ በኋላ ጨምሮ የተናገረው ንግግር ምንኛ ድንቅ ነው? ... " ከዚህም በላይ ደግሞ የአምላኬን ቤት ስለወደድሁ ለመቅደሱ ከሰበሰብሁት ሌላ የግል ገንዘቤ የሚሆን ወርቅና ብር አለኝና እነሆ ለአምላኬ ቤት ሰጥቼዋለሁ " 1ኛ ዜና 29 ፦ 1 - 6 ... መስጠት እንዲህ በመረዳት ሲሆን የተወደደ ፤ ዋጋውም እጅግ የበዛና ያማረ ይሆናል ፤ ቅዱስ ጳውሎስ " በደስታ ይስጡ እንጂ በግድ አይሆንም ፤ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና " 2ኛ ቆሮ 9 ፦ 7 እንዳለ። ...
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይኼው ሐዋርያ ይህ የመስጠትና የመቀበል ሥሌት ካልገባቸው የቆሮንቶስ ሰዎች ምናምንቴ እንዳልተቀበለ ፤ ዛሬም ካህናት አባቶች ፣ መምህራነ ቤተክርስቲያን ሥሌቱ ካልገባቸው ምዕመናን አንዳች ባይቀበሉ ፤ ስጡም በማለት አጥብቀው ባይለምኗቸው የተሻለ ነው። ... ምክንያቱም ከትክክለኛው የመስጠትና የመቀበል ሥሌት የተነሳ ያልሰጡ እንደሆነ ፤ መስጠታቸው የጽድቅን ፍሬ በማብዛት ፈንታ በአእምሯቸው ክፉ ሀሳብ እንዲመላለስ ያደርጋልና ነው ፤ ... ምናልባትስ ካህናቱንና መምህራኑን አንዳች ሰውኛ ጥቅም አሳዳጅ አድርገው ቢያስቡ? .... ምናልባትስ ... ሐዋርያው " እናንተን አገለግል ዘንድ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተቀብዬ ለምግቤ ወሰድሁ ከእናንተ ዘንድ በነበርኩበት ጊዜም ስቸገር ገንዘባችሁን አልተመኘሁም ፤ ባልበቃኝም ጊዜ ወንድሞቻችን ከመቄዶንያ መጥተው አሟሉልኝ ፤ በእናንተም ላይ እንዳልከብድባችሁ በሁሉ ተጠነቀቅሁ ፤ ወደፊትም እጠነቀቃለሁ " 2ኛ ቆሮ 11 ፦ 7-12 ማለቱ ይህንን አያመለክትምን? ... እንዲህም እንኳ ሆኖ ቅዱስ ጳውሎስ በወንጌል አገልግሎቱ ፤ ሥሌቱ ካልገባቸው ከእነዚህ የቆሮንቶስ ሰዎች አስተዋፅዖ ባይቀበልም ቅሉ ስለመስጠትና የመቀበል ሥሌት ደጋግሞ ያስተምራቸው እንደነበረ የጻፋቸው መልዕክታት እማኞች ናቸው። " በረከትን እንደምታገኙበት እንጂ በንጥቂያ እንደተወሰደባችሁ አይሁን ፤ አሳንሶ ለሚዘራ ለእርሱ እንዲሁ መከሩ ያንስበታል ፤ በብዙ የሚዘራ ግን ብዙ ያመርታል ፤ ... ለብዙ ሰዎች ስለሰጣችሁም የእግዚአብሔር ምስጋና በምታደርግላችሁ ልግስና ሁሉ ባለፀጋ ትሆናላችሁ " 2ኛ ቆሮ 9 ፦ 6 ... እንዲህም ስለሆነ የቤተክርስቲያን ካህናትና መምህራን ፤ ምዕመናን ሥሌቱን እንዲረዱት ፤ ገብቷቸውም መስጠታቸው የጽድቅን ፍሬ ማብዛት እንዲችል ሊያስተምሯቸው ይገባል።
አንዳንድ ምዕመናን የመስጠትና የመቀበልን ሥሌት ባለመረዳታቸው ምክንያት ከመስጠታቸው ሊያገኙት የነበረውን በረከት ከማጣታቸው ባሻገር ፤ በካህናትና በመምህራነ ቤተክርስቲያን እንዲሰጡ ስለተጠየቁ ሲከፋቸውና ሲያማርሩ ፤ መጠየቃቸውንም አንዳች የማይገባ ነገር አድርገው ሲናገሩ ይሰማሉ። ... በመጀመሪያ እኒህ አካላት ያላስተዋሉት ነገር በቤተክርስቲያን አውደምህረት ላይ እንዲሰጡ ሲጠየቁና ሲለመኑ እያማረሩ ያሉት ፤ እነርሱም ወደ ቤተክርስቲያን የሄዱት ሊለምኑ መሆኑን ነው ፤ ባገርኛ አባባል ' እንኩን ያላወቅሽ ስጡኝን ማን አስተማረሽ ' እንዲባል። ... ሌላው በዚህ ሀላፊና ጠፊ በሆነ ምድር ገዥዎቻችን የሆኑ አካላት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ጥረን ግረን ካገኘነው ላይ ድርሻ ኖሯቸው የሚወስዱ ከሆነ ፤ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የሚመሩን ካህናትና የቤተክርስቲያን መምህራንማ እንዴታ! ቅዱስ ጳውሎስ እኒህን የመሰሉትን ሰዎች በገሰጸበት አንቀፅ " ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋውንስ ጠብቆ ወተቱን የማይጠጣ ማን ነው? ... የሙሴ መጽሐፈ ኦሪትስ እንዲህ ብሎ የለምን? ' እህልን በምታበራይበት ጊዜ የበሬውን አፉን አትሰረው ' እንግዲህ ይህን የጻፈ እግዚአብሔር በሬ አሳዝኖት ነውን? ይህን የሚለው ፈፅሞ ስለኛ አይደለምን? የሚያርስ በተስፋ ሊያርስ የሚያበራይም በተስፋ ሊያበራይ እንደሚገባው በእውነት ስለ እኛ ተጽፏል ፤ እኛ መንፈሳዊውን ነገር ከዘራንላችሁ ስጋዊውን ነገር ብናጭድ ታላቅ ነገር ነውን? በእኛ ሹመት ሌላ የሚቀድመን ከሆነ የሚሻላችሁን እናንተ ታውቃላችሁ ፤ እኔ ይህን አልፈለግሁትም ፤ ነገር ግን የክርስቶስን ትምህርት እንዳላሰናክል በሁሉ እታገሳለሁ " 1ኛ ቆሮ 9 ፦ 7-13
ለአንክሮ ለተዘክሮ ያህል የመስጠትና የመቀበል ሥሌት የገባቸውና ይህንንም ሕይወት አድርገው የኖሩ ፣ የተጠቀሙበትም ሰዎች እነሆ ፦
በ1ኛ ነገስት በምዕራፍ 17 ታሪኳ ሰፍሮ የሚገኘው የሰራጵታዋ መበለት በነብዩ በኤልያስ ትዕዛዝ በእግዚአብሔር አምላክም ፈቃድ ምድሪቱ ለሦስት ዓመታት በድርቅ በተመታችበት ዘመን ፤ የሚያረካ ያህል የሚጠጣ ፤ የሚያጠግብ ያህል የሚበላ በቸገረበት ዘመን ፤ ለእግዚአብሔር ነብይ ፤ ለኤልያስ ውሃ ቀድታ በማጠጣቷ ፤ ከልጇ ጋር በልታት ልትሞት ከነበረችው ጥቂት ዱቄት ፤ አስቀድማ እንጎቻን ጋግራ በመስጠቷ ፤ ... ያላትን ስለሰጠች ፤ የተቀበለችው ውሃዋ እና እንጎቻዋ ሊያመጡላት የማይችሉትን ታላቅ ነገር ነበር። ይህች ሴት ነገ ነገወዲያ አምላኩን ጠይቆ ይሞላልኛል ብላ ተስፋ እንዳታደርግ እንኳ ፤ ኤልያስ የእግዚአብሔር ነብይ መሆኑን ሳታውቅ ያላትን ፤ የቻለችውን ስለሰጠች ... ያንን የችግር ዘመን በቤቷ አንዳች ሳይጎድል አለፈች ... ይህም ብቻ ያይደለ በሰው ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የማይችለውን እግዚአብሔር ሰጣት ... በኋላ ጊዜም የሞተ ልጇን ወደ ሕይወት መለሰላት። ... በሌላም ክፍል በዘፍጥረት በምዕራፍ 12 ታሪኩ ተጽፎ የሚገኘው ፤ አባቶች ድንግል እምነት ነበረችው በማለት ምስክርነታቸውን የሚሰጡለት ፤ አበ ብዙሃን አብርሃምስ ሟች ልጁን መስዋት አድርጎ በማቅረቡ ( በመስጠቱ ) ከእግዚአብሔር የተቀበለው ነገር ምንኛ ታላቅ ነው? ... አስቀድሞ የይስሃቅ አባት ይባል ነበረ ፤ አሁን ግን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ተባለ። '' የዳዊት ልጅ ፣ የአብርሃምም ልጅ ፤ የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጸሐፍ " ማቴ 1 ፦ 1
እንግዲህስ ... የመስጠትና የመቀበል ሥሌታችንን እናስተካክል ፤ አባቶች ' የዘራ ገበሬ ለዘር ያህል አያጣም ' ይላሉ ... ዘርቶ ቢተወው ፣ ባያርመውና ባይኮተኩተው እንኳን ከአረሙ ጋር አለፍ አለፍ ብሎ የሚበቅል አይታጣበትም ሲሉ ... ስለሆነም መስጠታችን ያለዋጋ የሚቀር አይደለም ... ቢሆንም መስጠታችን ካልቀረ ፤ ጥቂት መስጠታችን ብዙ እንደሚያስገኝልን ፤ ገንዘብን በመስጠታችን ገንዘብ ሊያመጣውና በሰው አእምሮ ሊታሰብ የማይችለውን እንደሚያሰጠን ፤ ከማመን ጋራ እንስጥ ፤ እግዚአብሔር እንደሁ በረከቱ አያልቅበት ....
" ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው። " ሥራ 20 ፦ 35
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
09/01/2003
Tromso, Norway
ምንጭ ፡ ዲ/ን ብርሃኑ አድማሴ ነሐሴ 15/2002 በ Norway, Stavanger ከተማ ያስተማረው ትምህርት
No comments:
Post a Comment