መዝሙረ ዳዊት

" እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ብፁዕ ነው። " መዝ 32 ፦ 12

Tuesday, June 29, 2010

የሕሊና ሕግ

የሕሊና ሕግ

የንስሐ አባቴ ልጆቻቸውን ሰብስበው የማስተማር በጎ ልማድ አላቸው ፤ ታዲያ ተሰባስበን በምንማማርበት በአንድ ወቅት ፤ እንወያይበት ዘንድ አንድ ርዕስ አንስተው ነበር " የአንድ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር መለኪያው ምንድን ነው? " የሚል ... በወቅቱም ከአንድ ወንድሜ እና ከሦስት እህቶቼ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ ከተወያየን በኋላ የንስሐ አባታችን የሰጡት ማጠቃለያ በተለይም ሕሊናን የተመለከተው በአእምሮዬ ሲመላለስ የከረመ ነበርና ብዕሬን አነሳሁ።

የንስሐ አባታችን ለውይይቱ ማጠቃለያ የሰጡት " የአንድ ክርስቲያን ሥነ-ምግባር የሚለካው ፤ የሚመዘነው ከፈጣሪው ብሎም ከመሰሎቹ ጋር በሰላምና በፍቅር ሊኖርበት ከተሰሩለት ሕግጋት አንጻር ነው። " በማለት ነበር። በርግጥም አባቶቻችን እንዳስተማሩን፦ እግዚዘብሔር አምላክ መንፈሳዊ አቅጣጫ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ፣ የሰው ልጅ በመልካም ጎዳና ተጉዞ በነፍስም በሥጋም እንዲጠበቅና እንዲጠቀም ፣ ርሥት አድርጎ የሰጠውን መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርስ ፣ እንዲሁም በየእለት ተለት እንቅስቃሴው ሁሉ አምላኩ ያደረገለትን ውለታ እንዳይረሳ ሕግን ሰርቷል። ... በዚህም ሰው ሕገ-እግዚአብሔርን በመጠበቁ እና ባለመጠበቁ በዚህ ይለካል። ዘጸ 20፦18
በሁለተኛ ደረጃ ከመሰሎቹ ጋር በመከባበር እና በመቻቻል በፍቅር ለመኖር በምድራውያን ሰዎች ... በቅዱሳን አባቶች ... በመንግስታት ... ለተሰሩ ሕግጋት እየተገዛ ይኖራል ፤ እነዚህም ሕግጋት የተጻፉ እንዲያም ሲል ማህበረሰቡ አብሮ በመኖር ሂደት ውስጥ የሚጠብቃቸውና የሚኖርባቸው ወጎች እና ልማዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ቅዱስ ጳውሎስ " የአባቶቼን ሕግ ተማርሁ " እንዳለ ሐ.ሥ 22፦3 ታዲያ ከዚህ የተነሳም የሰው ልጅ እነዚህን ሕግጋት በመጠበቁ የሥነ-ምግባሩ ደረጃ ይታወቃል ፤ አልፎ ተርፎም የፈጠረውን እግዚአብሔርን ያስመሰግንበታል። ... እከሌ ... እንዴት ያለ የተባረከ ... የእግዚአብሔር ሰው ... እከሊት ... አቤት ሥነ-ሥርዓቷ ... ያስብላልና።
ንስሐ አባታችን በሦስተኛና በስተመጨረሻ ያስቀመጡት እና ብዕሬን እንዳነሳ ያነሳሳኝ ደግሞ የሕሊና ሕግ ነው። አባታችን፦ ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በላከው መልዕክቱ " ስለዚህ ቁጣን ስለመፍራት ብቻ አይደለም ፤ ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። " በማለት ያስተማረውን ትምህርት በማስቀደም ሕሊናን የገለፁት እንዲህ በማለት ነበር " ሕሊና፦ እግዚአብሔር አምላክ መልካምን ከክፉ ይለይበት ዘንድ ለሰው ልጅ የሰጠው ከሥጦታዎች ሁሉ በላይ የሆነ ሥጦታ ነው። " ትምህርታቸውን በምሳሌ ሲያፀኑም ታሪኩ በዘፍ 3፦9 ላይ ተዘግቦ የሚገኘውን ቃየንን በማንሳት እንዲህ አሉ " ቃየን ወንድሙ አቤልን በግፍ ከገደለ በኋላ ሥለ ወንድሙ በተጠየቀ ጊዜ ' የወንድሜ ጠባቂ ነኝን? ' ማለቱ በጊዜው የተፃፈ ሕግ በመኖሩ ፤ ከዛ የተነሳ ሳይሆን ከሕሊናው ወቀሳ በመነጨ ነው። ''
በርግጥም ከየትኛውም በጎም ይሁን ክፉ ተግባር በኋላ ስለፈጸምነው ተግባር መልካምነት ወይንም ጥፋትነት የመጀመሪያ ማረጋገጫ የሚሰጠን ሕሊና ነው ፤ ምንም እንኳን የሕሊናን ወቀሳ የማድመጥ እና ያለማድመጥ ጉዳይ በሌላ ፈርጅ የሚነሳ ቢሆንም ... ታዲያ ሕሊና ወቀሳን በሚያስተላልፍበት ወቅት ለወቀሳው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ወቀሳ ከቀረበበት መጥፎ ተግባር በመታረም ፤ ከንስሐ አባቶቻችን ጋር ለነገ ሳንል የምንወያይበት ሁኔታ ቢፈጠር ከጥፋት የምንጠበቅ ሲሆን ... በተቃራኒው የምንሄድ ከሆነ ደግሞ ጥፋትን በራሳችን ላይ እንደመጥራት የሚቆጠር ይሆናል። " ሕግ የሌላቸው አሕዛብስ እንኳ ለራሳቸው ሕግን ይደነግጋሉ ፤ በሕጋቸውም የታዘዘውን ያደርጋሉ ፤ በልባቸው የተፃፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ ፤ ከሥራቸውም የተነሳ ይታወቃል ፤ ሕሊናቸውም ይመሰክርባቸዋል ፣ ይፈርድባቸዋል። '' ሮሜ 2፦14 ተብሎ እንደተፃፈ።
ፍርድ፦ የእግዚአብሔር ነው ፤ ቢሆንም እርሱ በሰጠን ሕሊና በመጠቀም እከሌ እንዲህ ነው ፤ እከሊት ደግሞ እንዲህ ናት ማለታችን በራሱ ሕሊናችን ለክፉ እና ደግ እውቅና ያለው ስለመሆኑ ማሳያ ነው። ... " ታዲያ ወንድሞቻችን ሆይ ልባችን የማይወቅሰን ከሆነ፦ በእግዚአብሔር ዘንድ መወደድ አለን? የምንለምነውንስ ከርሱ እናገኛለን? " 1 ዮሐ 1፦21 እንግዲህ በሕሊናዬ ሲመላለስ ስለነበረው ጉዳይ ይህን ያህል ካልኩ ዘንዳ ክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ብርሃነ ኅሊና በተሠኘ መጻሐፋቸው በገፅ 91 ላይ ባሠፈሩት ግጥማቸው ጽሑፌን ላብቃ።
'' ደግና ክፉውን እየደባለቀ
መንፈሱ ለይቶ ፍርድ ካላወቀ
ድካሙ ከሆነ ለጌጡ ለልብሱ
ልፋቱ ከሆነ እንዲሞላ ከርሱ
ካላቀረበለት ሕሊናው ወቀሳ
በምኑ ይበልጣል የሰው ልጅ ከእንስሳ? ''


4/4/2002
አ.አ

No comments:

Post a Comment